የሕገወጡ ሕወሓት መሪዎች ከ830 በላይ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤርትራ ወስደዋል – አሰፋ አብረሃ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕገወጡ ሕወሓት መሪዎች ከ830 በላይ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤርትራ ወስደዋል አሉ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የአስተዳደርና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈፃሚ አቶ አሰፋ አብረሃ፡፡
የባለአደራ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በመቐለ ከተማ ከተባበሩት መንግሥታት ልዑካን፣ ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ አሰፋ አብረሃ በዚሁ ወቅት፤ የሕገወጡ ሕወሓት መሪዎች በኤርትራ እንደሚገኙና ከ830 በላይ ተሽከርካሪዎችን ጭነው ወደ ኤርትራ እንደወሰዱ ገልፀዋል።
ተሽከርካሪዎቹ መወሰዳቸው የመንግሥት ተቋማት ሥራቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዳያከናውኑ ከፍተኛ እንቅፋት መሆኑንም አስረድተዋል።
የሕገወጡ ሕወሓት ቡድን ከሻዕቢያ ጋር በመተባበር በትግራይ ሕዝብና በክልሉ ላይ ከፍተኛ ውድመትና ኪሳራ ማድረሱን ገልጸው፤ የቡድኑ እንቅስቃሴ በክልሉ የሰላምና መረጋጋት ጥረቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንንም በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሕገወጡን ቡድን እንቅስቃሴ በግልፅ ሊያወግዝና በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አስፈላጊውን ጫና ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ባለአደራ አስተዳደሩ በተሰጠው የስድስት ወር የሥልጣን ጊዜ ገደብ ውስጥ ሰላምና ፀጥታን ማስፈን፣ የመንግሥት አስተዳደርና መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ ዋነኛ ተልዕኮዎቹ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ ማገገምን ማፋጠን፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስና ለምርጫ የሚያስፈልጉ ተቋማዊ ዝግጅቶችን ማጠናቀቅ ቀዳሚ ተግባራት መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍ ከባለአደራ አስተዳደሩ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ በነሐሴ ወር በተካሄደ ግምገማ መሠረት ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ወደ 700 ሚሊየን ዩሮ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ በመገንዘብ የድጋፍ ምላሹን እንዲያጠናክርና በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ እንቅስቃሴዎችን በግልፅ እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርበዋል።
በግዛቸው ግርማዬ