Fana: At a Speed of Life!

የአደባባይ በዓላት ለቱሪዝም ዘርፍ ማንሰራራትና ለዘላቂ ዕድገት መረጋገጥ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ብዝሃ ዘርፍ የልማት አቅጣጫን እየተከተለች የምትገኘው ኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት ብዙም አስታዋሽ ያልነበረውን የቱሪዝም ዘርፍም አንዱ የእድገቷ ምሶሶ በማድረግ አንፀባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡
በማንሰራራት ላይ ያለው የቱሪዝም ዘርፍ ማህበራዊ መስተጋብርን በማጠናከርና የሀገራችንን መልካም ገፅታ በማጉላት ከሚያበረክተው ትልቅ አስተዋፅዖ ባሻገር ከዘላቂ ልማት ግቦቻችን ጋርም የተናበበ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦችን በአግባቡ በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደ ሀገርም ሆነ በአዲስ አበባ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ልማቶቻችን አንዱ ለአንዱ ተመጋጋቢ መሆናቸውም ሁሉን አቀፍ ዕድገታችን እንዲፋጠን ምቹ መደላድል ፈጥሯል፡፡ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የህቡን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻል ባሻገር ለአደባባይ በዓላት ደማቅ አከባበር ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡
የአደባባይ በዓላት ከባህላዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ህዝባዊ እሴቶቻቸው ባሻገር ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸውም ቀላል አይደለም፡፡
የአለባበስ፣ የአመጋገብ እንዲሁም የውበት አጠባበቅ ስርዓቶች ልዩ ልዩ ባህሎች ጎላ ብለው የሚታዩባቸው የሀገራዊ እሴቶች ነፀብራቅ ሲሆኑ፣ የህዝብ ለህዝብ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርንም ያሳድጋሉ፡፡
በበዓላት ወቅት ገበያው ይሞቃል፣ ኢኮኖሚው ይነቃቃል። ከበዓላት ቀደም ብሎም በተለይም የባህላዊ አልባሳት ግብይት ጎልቶ ይታያል። ባህላዊ ምግቦችን ለማዘጋጀት የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎችን መገበያየትም በዚህ ወቅት ከፍ ይላል።
ከቤተሰብ ፍጆታ ባሻገር ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት የማዕድ ማጋራት ፕሮግራምም በበዓላት ወቅት ሰፋ ብሎ ይስተዋላል።
በዓላት ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚጠናከሩባቸው በመሆናቸው የእንኳን አደረሳችሁ ልዩ ልዩ ስጦታዎችም በዓልን አስመልክቶ በስፋት ይከናወናሉ። በዓላትን ለማክበር የሚሰባሰቡ ተሳታፊዎች የበዓሉን አከባበር ትዝታ የሚያስታውሷቸውን ባህላዊ ቁሳቁሶች መገብየትም በስፋት የተለመደ ነው፡፡
የቅርቡም የሩቁም የሚገናኝባቸው የበዓላት ወቅቶች የእርስ በእርስ ትውውቅን እና ትስስርን ስለሚያጠናክሩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩ ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የአደባባይ በዓላት ዋነኛ የስዕበት ማዕከላት በመሆናቸው ለቱሪዝም ዘርፉ ማንሰራራት የማይተካ ሚና ይጫወታሉ። ለአብነትም በመስቀል ደመራ እና በኢሬቻ በዓላት በሚሊየን የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ ዜጎች ብቻም ሳይሆን በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችም ስለሚገኙ የከተማችንም ሆነ የሀገራችን ኢኮኖሚ በእጅጉ ይነቃቃል።
የበዓላቱን ስሜት ለመጋራት ከሚሸማምቷቸው ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች በተጨማሪ ለሆቴሎች እና ለሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቀላል የማይባል የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገራችን የሚገባበት ዕድልም ሰፊ ነው፡፡
የበዓላቱ ተሳታፊዎች መዲናችንን እና ሀገራችንን ማስተዋወቅ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ስለሆኑ በየዓመቱ የጎብኝዎች ቁጥር እያደገ ይመጣል፣ የቱሪዝም ዘርፉ ይበልጥ ያንሰራራል፤ የሀገራችን ዕድገትም ፈጣንና ዘላቂ እንዲሆን ጉልህ ሚና ይጫወታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.