የሕዳሴ ዋንጫ የራስ አቅምና የመስዋዕትነት ዐሻራ ነው – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስአበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዳሴ ዋንጫ የራስ አቅምና የመስዋዕትነት ዐሻራ ነው አሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር።
የሕዳሴ ዋንጫ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በክብር እንዲያርፍ በፌደሬሽን ምክር ቤት እና በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካከል በዛሬው ዕለት ርክክብ ተካሂዷል።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በመድረኩ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፣ የሕዳሴ ዋንጫው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መልኮች፣ በተለያዩ አቅሞችና በተለያዩ መንገዶች ያበረከቱትን የጋራ ዐሻራ የያዘ ነው።
ዋንጫውየዚህ የጋራ ታሪክ አካል ነው ያሉት አፈ ጉባኤው፣ በመላው ሀገራችን ከልጅ እስከ አዋቂ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ፣ በጊዜውና በመሳሰሉት አሻራውን ያኖረበት ታሪካዊ ምልክት ነው ብለዋል።
ዋንጫው የብዙ ሚሊየኖችን ተሳትፎ፣ መስዋዕትነት፣ የጋራ ቁርጠኝነትንና የአንድ ሕዝብን የጋራ ተስፋ የሚያመለክት መሆኑን ተናግረዋል።
ዋንጫውየግድቡን የግንባታ ታሪክ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን በአንድ ዓላማ ዙሪያ ሲቆሙ ምን ማድረግ እንደሚችሉ የሚያሳይ የአንድነት ምልክት ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሰንደቅ ዓላማችን ታጅቦ ዋንጫው ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ሲዘዋወር የአንድነት መልዕክትን ከአንዱ ወደ ሌላው የሚያስተላለፍ የጋራ አምባሳደር ነው ሲሉም አንስተዋል።
በርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዳይሬክተር ዮሴፍ በቀለ (ዶ/ር) ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ከሰኔ 2005 እስከ ነሐሴ 2017 ዓ.ም የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በመላው ሀገሪቱ በማዘዋወር በቦንድ ግዥ እና በስጦታ ከ6 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ሃብት ማሰባሰብ ተችሏል።
ላለፉት 14 ዓመታት ከህብረተሰቡ በአጠቃላይ የተሰበሰበው ገንዘብ ከ25 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ሲሆን ለግድቡ ግንባታ ከዋለው ጠቅላላ ወጪ 10 በመቶ የሚሆነው ከህዝቡ የተሰበሰበ መሆኑ ይታወሳል።
በመሳፍንት እያዩ