Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ አፍሪካ ሚዛን አስጠባቂነት ሚናዋን ያጠናከረችው ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ባላት ታሪካዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ የበላይነት የቀጣናው የሃይል ሚዛን አስጠባቂ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላም፣ ልማት እና መረጋጋት ከኢትዮጵያ ጥንካሬ እና ሰላም ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው፤ የቀጣናውን ሁለንተናዊ መስተጋብርም ያለ ኢትዮጵያ ማሰብ አይቻልም፡፡

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ መሪ ከሆነችባቸው ዘርፎች አንዱ በቀጣናው ያላት የደህንነት ሚና ነው፤ ሀገሪቱ የቀጣናው ሰላምና ጸጥታ ምሰሶ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለች ሀገር ስትሆን በተለይም በሶማሊያ አል ሸባብን ለመዋጋትና የጸጥታ ዋስትና ለመስጠት በሰላም አስከባሪነት ግንባር ቀደም ሚና ስትጫወት ቆይታለች።

በደቡብ ሱዳንና በሱዳን የሚከሰቱ የውስጥ ቀውሶችን በንግግርና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በኢጋድ እና በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ውስጥ የአደራዳሪነትና አስታራቂነት ሒደት ውስጥ ሚናዋ ከፍተኛ ነው፡፡

የኢኮኖሚ እና የመሠረተ ልማት ትስስር ወይም የኢነርጂ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ መሪነት ሌላው ማሳያ ነው፡፡

በተለይም በታዳሽ ኃይል አቅርቦ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ማለትም ለሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ቀጣናዊ ትስስርን በተግባር እያጠናከረች ትገኛለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሀገር ውስጥ ብርሃን ከመሆን አልፎ ለቀጣናው ሀገራት የሚተርፍ ንጹህ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት በማመንጨት የምስራቅ አፍሪካን የኢንዱስትሪ መነቃቃት የሚያግዝ ትልቅ የልማት ሞተር ሆኗል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ማዕከል ናት፡፡ ለዚህም አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ መሆኗን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተደማጭነት ማደጉ በቀጣናው ላይ ያላትን የፖለቲካ የበላይነትና የድምፅ ክብደት ከፍ አድርጎታል።

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃና በደን እንክብካቤ እያከናወነችው ያለው ተግባር በምስራቅ አፍሪካ የሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናዎችን እና ድርቅን ለመቋቋም ለጎረቤት ሀገራት እንደ ትልቅ ተሞክሮና አርአያነት እየተጠቀሰ ይገኛል።

ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብና እያደገ የመጣ ምጣኔ ሃብት ያላት ሀገር በመሆኗ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ያላት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ወሳኝ ሀገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መረጋጋትና ጥንካሬ ለጠቅላላው የምስራቅ አፍሪካ ሰላም፣ ደህንነት እና የኢኮኖሚ እድገት ዋነኛና ቁልፍ ነው፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.