ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር እንሰራለን – የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ የተሾሙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በኢትዮጵያ እና በሀገሮቻቸው መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንሰራለን አሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ አምባሳደር አብደላ ሀሰን በሁለቱ ሀገራት መልካም የሆነ ግንኙነት መኖሩን አንስተው፤ ይህን ግንኙነት በሁሉም መስክ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የቆጵሮስ አምባሳደር ሳቫስ ቭላድሚሩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለቆጵሮስ ሪፐብሊክ ጠንካራና ታማኝ አጋር እንዲሁም ጥሩ ወዳጅ ሆና ዘልቃለች።
በቆጵሮስና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የባህል፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማሳደግ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማስፋት እንደሚሰሩ ነው የገለጹት።
የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጃን ሮሴክ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በተለያዩ መስኮች ትብብርን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ስራዎችን እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በቀጣይም የህፃናት ሙዚየምን ጨምሮ በመከላከያና ደህንነት እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንሰራለን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር መሆኗን የገለጹት ደግሞ የአየርላንድ አምባሳደር ሲያላራን ማደን ናቸው፡፡
ሁለቱም ሀገራት ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው የጋራ የንግድና የኢኮኖሚ ዕድሎች ላይ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በባህል ዘርፍም በጋራ እየሰራን ነው፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ በአየርላንድ ከታወቁ የአጫጭር ልቦለድ መጻሕፍት አንዱን ወደ አማርኛ ተርጉመን እናስመርቃለን ብለዋል።
በቅድስት አባተ