Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ – ታላቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፡ የሀገረ መንግሥት ግንባታ እና የሉዓላዊነት ዘብ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ታሪክ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገረ መንግሥት ህልውና፣ የሉዓላዊነት እና የፅናት ዋና አምድ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል።
ባለፉት ዘመናት በሀገሪቱ ላይ በተፈራረቁ የፖለቲካ ስርዓቶች ውስጥ ሠራዊቱ የከፈለውን የህይወት መስዋዕትነት በማሳነስ ተቋማዊ ስብራቶች እንዲደርሱበት የመደረጉ እውነታ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ የተከናወኑ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች የሠራዊቱን ምልከታ እና ቁመና ወደ አዲስ የልህቀት ደረጃ አሸጋግረውታል።
የቀድሞ የመከላከያ አባል እና የአሁኑ የክብር አባል መስፍን ፈይሳ፤ ኢትዮጵያዊነት በቃላት ሳይሆን ለሀገር በሚከፈል ዋጋ የሚለካ እንደሆነ ገልጸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም ይህንኑ በተግባር የሚያሳይ የጀግንነት ምልክተ መሆኑን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ወታደር ከዓለም አቀፍ የውትድርና እሳቤዎች በእጅጉ የተለየ መሆኑን በማንሳት ሀገሩን ከምንም በላይ አብልጦ የሚወድ እና በጽኑ ፍቅር እሳት ውስጥ ለመግባት የማይመለስ የጽናት ማሳያ እንደሆነ ያብራራሉ።
ሠራዊቱ ይህ ጥልቅ የሀገር ፍቅር መሠረት ባይኖረው ኖሮ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ከውስጥ እና ከውጭ በተሰነዘሩባት የጠላት ጥቃቶች ሳቢያ ህልውናዋ አደጋ ላይ ይወድቅ እንደነበርም ያስረዳሉ።
በታላቅ የሀገር ፍቅር የሉዓላዊነት መከታ ሆኖ በዘለቀው ሠራዊት ውስጥ የተካሄደው የለውጥ ጉዞ የዘመናትን ክፍተት የደፈነ ተቋማዊ እመርታ ነው።
ቀደም ሲል የነበሩት ውጊያዎች በሰው ኃይል ብዛት እና በሚከፈል ከፍተኛ መስዋዕትነት ላይ የተመሠረቱ የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ያለው የመከላከያ ቁመና ግን በቴክኖሎጂ የጎለበተ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታዘ፣ በድሮን እና በዘመናዊ የውጊያ ጥበቦች የተገነባ ነው።
ይህ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ተቋም የሠራዊቱን የመፈጸም አቅምና እና የሀገርን ድንበር የመጠበቅ ብቃት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
መስፍን ፈይሳ እንደሚሉት፤ በድሮ አስተሳሰብ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩ ታሪካዊ ጠላቶች እና የውስጥ ባንዳዎች ሙከራ የሠራዊቱን አዲሱን የቴክኖሎጂ አቅም እና ዝግጁነት ያላገናዘበ የከንቱ ቅዠት ነው።
መከላከያ ሠራዊቱ የሀገርን ድንበር ከመጠበቅ ባለፈ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ የሜጋ ፕሮጀክቶች መሳካት አስተማማኝ ደጀን ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡
ጠንካራ ሠራዊት መገንባት የሀገሪቱን የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገት የሚያስቀጥል፣ የባህር በር እና ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማሳካት በፅኑ መሠረት ላይ የሚያቆም ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑንም ያብራራሉ።
በዘመናዊና ቴክኖሎጂ መር አቅም የተገነባው ይግ ተቋም ሀገሪቱ ወደተሻለ የልማትና የብልጽግና ከፍታ እንድትሸጋገር ዋስትና ከመሆኑም በላይ የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ ለማክሸፍ የሚያስችል አስተማማኝ የሉዓላዊነት ዘብ ሆኖ ይቀጥላል።
በዮናስ ጌትነት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.