Fana: At a Speed of Life!

ሉዓላዊነትን የመጠበቅና የማጽናት ውሳኔ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በትናንትናው ዕለት በአስመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት ወስናለች። ከዚህም በተጨማሪ 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ ከኢትዮጵያ እንዲወጡም ተወስኗል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም አንድ የግብጽ ዲፕሎማት በተመሳሳይ 48 ሰዓት ውስጥ ኢትዮጵያን ለቅቆ እንዲወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።

ውሳኔው የተላለፈው በድንገት አይደለም። ለረጅም ጊዜ በአብሮ መኖር፣ በጋራ ልማትና በሰላማዊ ቀጣና ላይ የነበረው ትዕግስት ሲዳከም፣ የደህንነት ስጋቱም ሲጨምር የተወሰደ ጠንካራና ሉዓላዊ ርምጃ ነው።

ዓለም አቀፍ ህግ በግልጽ ይደነግጋል፡ ማንኛውም ሀገር የሉዓላዊነት ጥያቄ ሲፈጠርበት  ራሱን የመከላከል ሙሉ መብት አለው።

ይህ መርህ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ውስጥ የተካተተ፣ በዓለም አቀፍ ልማድ የተረጋገጠና በሉዓላዊ እኩልነት ላይ የተመሠረተ ነው።

የውጭ ኃይሎች በሀገር ውስጥ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት፣ የዲፕሎማቶችን ሽፋን በመጠቀም የሚፈጽሙት ተግባር፣ የቪየና የዲፕሎማሲ ስምምነትን የሚጥስ እንቅስቃሴ የሉዓላዊነት ጥቃት ነው።

ኢትዮጵያም ይህን ጥቃት የመከላከል ህጋዊና ሥነ-ምግባራዊ መብት አላት። መብቷንም በተግባር አሳይታለች።

ፈርኦኖቹ አንገቷን ቀና ያደረገች፣ በራሷ ፍላጎት የምትመራ ኢትዮጵያን ማየት አይፈልጉም። የዓባይን ውሃ ለሕዝቧ ልማት መጠቀም የጀመረችን፣ የባሕር በር ጥያቄዋን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የምታስቀርብን፣ በቀጣናው ውስጥ የራሷን ድምፅ የምትሰማ ኢትዮጵያን እንደ ስጋት ይቆጥሯታል።

ሻዕቢያ ደግሞ በዚህ አጀንዳ ላይ በርካሽ ዋጋ የሚሠራ ተላላኪ ሆኖ ቆይቷል። በሀገር ውስጥ ያሉ ሽፍቶችን እያቀናጀ፣ የጦር መሣሪያና የሎጂስቲክስ ድጋፍ እያደረገ፣ የሰላምና የደህንነት መሠረቶችን ለማናጋት እየሠራ ያለ ኃይል ነው።

ይህ እርምጃ የጥላቻ ወይም የበቀል አይደለም። የራስን ሕልውና የማረጋገጥ፣ የሕዝብን ሰላም የመጠበቅና የቀጣናውን መረጋጋት የማረጋገጥ ኃላፊነት ነው።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ያላት ታሪካዊ፣ ባህላዊና የሕዝብ-ለሕዝብ ግንኙነት አይረሳም። ነገር ግን መንግሥታዊ ጠብ አጫሪነትና መንግሥታዊ ሽብርተኝነት ከሰላማዊ ግንኙነት ጋር አይጣጣምም።

ፈርኦኖችና ተላላኪዎቻቸው ኢትዮጵያን እንደደከመች፣ እንደተበታተነችና እንደተናጋች ለማሳየት ይጥራሉ። ግን ታሪክ እንደሚመሰክረው፣ ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ጊዜ ሁሉ አንገቷን አቀናች። ዛሬም እንደዚያው ነው። የሉዓላዊነቷን ጥበቃ በጠንካራ ቃልና በተግባር ታረጋግጣለች።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.