ሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ የኦሮሞን ህዝብ ታላቅነትና ለሃገር ያለውን ፍቅር በድምቀት ያሳየ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ የኦሮሞን ህዝብ ክብር ፣ታላቅነት እና ለሃገር ያለውን ፍቅር በድምቀት ያሳየ ሆኖ ተጠናቅቋል አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ።
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል በድምቀት መጠናቀቁን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዓሉ የኦሮሞን ህዝብ ክብርና ታላቅነት እና ለሃገር ያለውን ጽኑ ክብር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
የዘንድሮው በዓል የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶችንና የሃይማኖት ድንበሮችን በማለፍ የኦሮሞ ህዝብ አንድነትን በጠንካራ መሰረት ላይ የገነባበት ታላቅ ምዕራፍ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
በሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ላይ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ህዝቦች ያሳዩት አንድነት ከምንጊዜውም በላይ የሚያስደንቅ ነው ያሉት።
አክለውም ዛሬ የታየው ይህ የህብረት ጥንካሬ፣ ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት መፈጠር ትልቅ ምሰሶ መሆኑን የሚያሳይ ግልጽ ማሳያ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ባህላዊ ክብርና አንድነታችንን በሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ እንዳሳየን ሁሉ ነገም በሆራ ሀርሰዴ ያህንኑ በድምቀት እንደግመዋለን ብለዋል።
በዓሉ በሰላም፣ በፍቅርና በመከባበር መንፈስ እንዲከበር ላደረጉ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ ለጸጥታ አካላት እንዲሁም ለሚዲያ ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ