አንድነት እና ህብረ ብሔራዊነት የተንጸባረቀበት ሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ሕያው መገለጫ ነው።
በዛሬው ዕለት ሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ “ኢሬቻ ለብሔራዊ መግባባት ” በሚል መሪ ቃል እሴቱን ጠብቆ በድምቀት ተከብሯል።
ኢሬቻ ከባህላዊ እሴቱ ባሻገር፣ የተለያዩ ሕዝቦች በፍቅርና በወንድማማችነት የሚገናኙበት፣ የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶቻችን የሚጎሉበት ታላቅ በዓል ነው።
ኢሬቻ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከውሃ ሙላት ወደ ፀደይ እና የአበባ ወራት መሸጋገሪያው መስከረም ወር ማብቂያ ላይ ሲከበር አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ ፎሌዎች፣ ወጣቶች እና የበዓሉ አክባሪ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተሰባስበው አምላካቸውን (ዋቃን )ያመሰግናሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን በአንድነት የበዓሉ ማክበሪያ ቦታ ሲያመሩ የሚታየው ህብር ውበቱ ቀልብ ሳቢ ነው፡፡ዛሬም በሆረ ፊንፊኔ ይህንኑ መልክ ጎልቶ ተንጸባርቋል።
ኢሬቻ ለኢትዮጵያውያን የአንድነታቸው ማጥበቂያ ገመድ ፣ ለአብሮነት እና ለጋራ ሰላም የሚሰባሰቡበት ለሀገራቸው ሰላም ፈጣሪያቸው የሚለምኑበት በዓል እንደመሆኑ፤የኢሬቻን እሴቶች በተግባር በመግለጽ፣ አቅሞቻችንን አስተባብረንና አንድነታችንን አጽንተን፣ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ለሀገራዊ መግባባትና ለሁለንተናዊ ብልጽግና በጋራ መትጋት ይገባል፡፡
በዓሉ በአባ መልካ ተከፍቶ በአባ ገዳዎች ተመርቆ በዓሉን ለማክበር በተሰበሰበው ሕዝብ በአንድነት ይከበራል።
በሆረ ፊንፌኔ ኢሬቻ በዓል ላይም አንድነት ፣ኢሬቻ ለሰላም ፣ኢሬቻ ለአብሮነት ፣ ኢሬቻ በጋራ ለሀገር ለመቆም ያለው ፋይዳ ተንፀባርቋል፡፡
መልካም በዓል
በእመቤት ሲሳይ