Fana: At a Speed of Life!

የሞቃዲሾ ድምፅ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ርዕይ !

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እውነት እና ፍትሃዊነትን መሰረት ያደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች ሲሰሙ መሸማቀቅን የሚመርጡ ወገኖች መኖራቸው ባይካድም፣ የታሪክና የህግ እውነታዎች ግን መቼም ቢሆን ተሸፍነው ሊቀሩ እንደማይችሉ የአደባባይ ምስክር እየተገኘላቸው ነው።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከአል አራቢያ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰጡት ምስክርነት ለዚህ ማሳያ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ በቀጥታ ከቀይ ባህር ጋር ባትዋሰንም፣ በአለም አቀፍ የውሃ ህጎች መሰረት የቀይ ባህር ተጋሪ ሀገር እንድትሆን የሚያስችላት ህጋዊ መብት እንዳላት በግልጽ መናገራቸው፣ በቀጣናው ለረጅም ጊዜ ሲሸረብ የነበረውን የፖለቲካ ሴራ ያፈረሰና አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ የከፈተ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህ የፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ አስተያየት፣ ኢትዮጵያ የብሄራዊ ጥቅሟንና የህዝቦቿን የልማት ፍላጎት ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት በትክክለኛ እይታ የተረዳች ጎረቤት መሆኗን የሚያሳይ ነው።

የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ የቅንጦት ወይም የፖለቲካ የበላይነትን የመፈለግ ጉዳይ ሳይሆን፣ የ130 ሚሊዮን በላይ ትልቅ ህዝብ የህልውና፣ የኢኮኖሚ ነጻነት እና የደህንነት ጥያቄ መሆኑን ቀጣናዊ ግንዛቤ እየተያዘበት መምጣቱን ያረጋግጣል።

በአለም አቀፍ የባህርና የውሃ ህጎች ላይ የተደገፈው ይህ ፍትሃዊ የዲፕሎማሲ አካሄድ፣ አሁን ላይ በአለም አቀፍ መድረኮችም ጭምር ተቀባይነትና እውቅናን እያገኘ መምጣቱን የፕሬዚዳንቱ ንግግር በግልጽ ያሳያል።

ይህ ስትራቴጂካዊ እውቅና የኢትዮጵያን ታላቅ ርዕይ እና የወደፊት የብልጽግና ምልከታ የሚያንጸባርቅ ነው። ኢትዮጵያ እንደ አንድ ትልቅ ሀገር በቀጣናው ያላትን የጂኦ-ፖለቲካዊ ሚና ለማሳደግ እና የህዝቦቿን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ የባህር በር ባለቤትነት ወይም የቀይ ባህር ተጋሪነት ወሳኝ መሆኑን ትረዳለች።

ይህ የባህር በር ወሳኝነት ጉዳይ በዘፈቀደ የሚነሳ ሳይሆን አለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካ ሳይንስ እና ምሁራን ያረጋገጡት እውነት ነው።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው አልፍሬድ ቴየር ማሃን በታዋቂው “The Influence of Sea Power Upon History” መጽሐፉ ላይ፣ የማንኛውም ሀገር ታላቅነት፣ የኢኮኖሚ ብልጽግና እና የአለም አቀፍ ተደማጭነት በቀጥታ የሚወሰነው የባህር በርን በመቆጣጠር ላይ መሆኑን ያስረዳል።

ማሃን እንደሚለው፣ የባህር በር የሌላቸው የየብስ ኃይሎች ምንም ያህል ትልቅ ቢሆኑም፣ ሁልጊዜም በባህር በር ባለቤቶች የኢኮኖሚ ከበባ እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ጥገኝነት ውስጥ ለመውደቅ ይገደዳሉ። በተመሳሳይ መንገድ፣ ኮሊን ፍሊንት በ2024 እ.ኤ.አ ባወጣው “Near and Far Waters: The Geopolitics of Seapower” በተሰኘው አዲስ ጥናቱ፣ የባህር በር ለአለም አቀፍ የንግድ ውድድር ዋነኛው ሞተር መሆኑን በመጥቀስ፣ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአቅራቢያቸው ባሉ የባህር ዳርቻ ሀገራት ፍላጎትና የፖለቲካ ውሳኔ ስለሚታጠሩ የራሳቸውን ብሄራዊ ጥቅም እና ታላቅ ርዕይ በነጻነት ለማስፈጸም ከፍተኛ መሰናክል እንደሚገጥማቸው ያረጋግጣል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለማደናቀፍ እና ሀገሪቱን በቀጠናው ለማግለል በካይሮ እና በአስመራ መዲናዎች ሲሸረብ የነበረው የሴራ ድራማ መበጣጠስ መጀመሩን ይህ አዲስ አዝማሚያ ይመሰክራል።

ለዓመታት ኢትዮጵያን የጥቃትና የግርግር ምንጭ አድርጎ በመሳል፣ የቀይ ባህር ጥያቄዋን ከቀጣናዊ ደህንነት ስጋት ጋር ለማገናኘት የተሰሩት የፕሮፓጋንዳ ስራዎች መሰረተ ቢስ መሆናቸው ተጋልጧል።

ካይሮ እና አስመራ በኢትዮጵያ ላይ የጋራ የከበባ ስትራቴጂ ለመዘርጋትና የቀጣናውን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ለማሰለፍ የሰፉት የሴራ ድር፣ በትልቁ ህዝብ ጽናት፣ በታላቋ ሀገር ህጋዊ መብት እና በእነዚህ አለም አቀፋዊ ሳይንሳዊ እውነታዎች የበላይነት ምክንያት እየተበጣጠሰ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና በህግ ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ ጉዞ ወደፊት መጓዙን እንደሚቀጥል ማሳያዎች እየበረከቱ ነው። የቀይ ባህር ተጋሪነት ጥያቄ ታሪካዊ ፍትህን፣ አለም አቀፋዊ ህግን እና ማሃንና ፍሊንት የመሰሉ ምሁራን ያስቀመጡትን ስትራቴጂካዊ እውነታ የተከተለ በመሆኑ፣ የቱንም ያህል የሴራ ድሮች ቢጎነጎኑም እውነቱ ከማሸነፍ ወደኋላ አይልም።

የቀጣናው ሀገራትም የኢትዮጵያን የህልውና ጥያቄ በአግባቡ በመረዳት፣ በትልቅ ህዝብ፣ በትልቅ ሀገር እና በታላቅ ርዕይ ላይ የተመሰረተውን የጋራ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት እቅድ በመቀበል፣ ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠር መተባበር ብቸኛውና ዘላቂው አማራጭ መሆኑን እየተገነዘቡት መጥተዋል።

በኃይለኢየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.