የጽናት ተምሳሌቷ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ የደገሱላትን የጥፋት ድግስ በጽናት እየመከተች የልማትና የሰላም ጉዞዋን በፅናጽ አስቀጥላለች።
ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱን ለማፍረስና አንድነቷን ለመበተን በርካታ የተቀናጁ ሴራዎችና ቢሞከሩም፣ በህዝቡና በመንግሥት ጠንካራ አንድነትና ጽናት ጥረቶቹን ማክሸፍ ችላለች።
የሀገር ውስጥ ባንዳዎች ከታሪካዊ የውጭ ጠላቶች ጋር በመሻረክ፣ ሀገሪቱን ወደማያልቅ የእርስ በርስ ጦርነትና ለመክተት ሰፊ ሙከራዎች ተካሂደው ነበር። ለዚህም ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዎች፣ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችና መጠነ ሰፊ የሚዲያ ፕሮፓጋንዳዎች ከየአቅጣጫው ተሰንዝሮባታል፡፡
ሆኖም ግን፣ እነዚህ የሀገር ማፍረስ ውጥኖች በህዝቧ አንድነት ሊከሽፉና ሊሸነፉ ችለዋል። የዚህ ታላቅ ድል ዋነኛው ምሥጢር የሕዝብና የመንግስት የማይናወጥ አንድነት ነው፡፡
በዚህ ረገድ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና መላው የጸጥታ መዋቅር ከሕዝቡ ያገኘው ያልተገደበ ሞራላዊና ቁሳዊ ድጋፍ የድሉ ዋነኛ መሠረት ሆኖ አገልግሏል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ እንደሚታወቀው ሁሉ፣ በሀገር ህልውና ላይ የመጣን አደጋ ለመመከት “አልደራደርም” በሚል በአንድ ድምፅ ከመንግሥት ጎን በመቆም አስመስክሯል።
ይህ በፈተና ወቅት ይበልጥ የሚጠነክረው የአንድነት እሴት፣ የጠላትን ስነልቦና በመስበር ሀገሪቱ ሉዓላዊነቷን አስከብራ እንድትቀጥል አስችሏታል።
ከሁሉ በላይ አስደናቂው ጉደይ ኢትዮጵያ በዚህ ሁሉ ታሪካዊ ፈተና ውስጥም እያለፈች የልማትና የኢኮኖሚ ጉዞዋን ለአፍታም አለማቆሟ ነው። ሌሎች ሀገራት በሰላም ጊዜ እንኳን ለማሳካት የሚቸገሩትን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ ሆና አሳክታቸዋለች፡፡
ለአብነት ያህል በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የተከናወኑትና እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ እና ደፋር የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ሀገሪቱን ከዕዳ ጫና በመታደግ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ መቋቋም አቅሟን ማሳደጓ ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ የሚያስተምረን አንድ ትልቅ እውነት አለ እርሱም የሕዝብና የመንግሥት አንድነት ሀገሪቱ ሚገጥማትን የውስጥም ይሁን ለውጭ ተግዳሮቶች በብቃት ለመመከትና ልማትና ሰላሟን ለማስቀጠል ወሳኝ መሆናቸውን።
ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በጽናት እየተሻገረች፣ የውስጥ አንድነቷን በማጠናከር ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ታሪካዊ ጉዞ አጠናክራ ትቀጥላለች።
በትዕግስት ግዛቸው