ሩጫ ሀገርን በመልካም ስም የሚፅፍ ብዕር
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አንዳንድ ሀገራት በጦር ኃይላቸው ይታወቃሉ፤ አንዳንዶቹ በሀብታቸው። ኢትዮጵያ ደግሞ ዓለምን በረጅም ርቀት ሩጫ ውድድር ታስደምማለች፡፡ ዓለም በቡናችን የሚውቀንን ያህል በታላላቅ ሯጮቻችን ያወቀናል፡፡
አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ የዓለምን የውድድር መድረክ ከተቆጣጠሩት ኮከብ አትሌቶቿ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በምታዘጋጀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ትታወቃለች፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ የህብረ ብሔራዊነት አንድነት መገለጫ ሆኗታል፡፡
እነሆ ዛሬም በድምቀት እና በግዝፈት በስኬት ተካሂዷል፡፡ ዛሬ ማለዳ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከ60 ሺህ በላይ ጥንድ እግሮች፣ ልዩ ልዩ ቀለም ያለው መለያ ለብሰው፣ በአንድ ልብ ሮጠዋል።
ታላቁ ሩጫ በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ውድድር ነው። ሁነቱ ሩጫ ብቻ አይደለም፤ የሀገር ውበት የሚገለፅበት አፍሪካዊ ስኬት ነው፡፡
በአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ አነሳሽነት የተጀመረው ይህ ውድድር፣ ከዓመት ዓመት እየተመነደገ፣ ከስፖርት ሜዳ አልፎ የሀገር መልካም ገጽታ መስኮት ሆኗል።
ባለሙያውም ጀማሪውም፣ ወጣቱም አዛውንቱም፣ ኢትዮጵያዊውም እንግዳውም በአንድ ልብ ይሮጣል። ሀገር በፖለቲካ ንግግር ብቻ አይደለም ራሷን የምታስተዋውቀው፤ በአንድ ልብ አንድ ላይ በሚሮጡ ከአስር ሺዎች በላይ ፈገግታም ጭምር።
ስፖርት የሀገር ገር ኃይል ነው። ምክንያቱም ሰዎች ሀገርን የሚወዱት በዜና ሳይሆን በትዝታ ነው።
ዓለም እጅግ አድርጎ የሚወደው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፣ ወይም የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ውድድር ሀገራቱ ተወዳጅነታቸውን የሚጠናክሩባቸው ቁልፍ የገፅታ መገንቢያ ሁነቶች ናቸው፡፡
ሯጮች ራሳቸው ተሳትፈው አይረሴ ትዝታ የሚያስቀሩበት እንደ ታላቁ ሩጫ ዓይነት ሁነቶች ደግሞ የተለዬ አቅም አላቸው፡፡ አንድ እንግዳ በአዲስ አበባ ጎዳና ሮጦ፣ ቡና ጠጥቶ ሲመለስ፣ ለዓመታት የሚያስቀረው መልም ትውስታ እና ታሪክ ይዞ ይመለሳል።
የታላላቅ አትሌቶች ምድር
ኢትዮጵያ የሯጮች ሀገር የሆነችው በአጋጣሚ አይደለም። በ1960 በሮም አደባባይ ባዶ እግሩን ሮጦ ማራቶንን ያሸነፈው አበበ ቢቂላ፣ ለአፍሪካ የኦሊምፒክ ወርቅ በር የከፈተ ስም ነው።
ከእርሱ በኋላ ደራርቱ ቱሉ፣ መሰረት ደፋር፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ሌሎች — እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ጀግና ወልዶ፣ ሠንደቁን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ አውለብልቧል።
እነዚህ አትሌቶች ሜዳሊያ ይዘው ብቻ አልተመለሱም፤ ለሚቀጥለው ትውልድ “እኔም እችላለሁ” የሚል ህልም ተክለው አልፈዋል።
ታላቁ ሩጫም ያንን ህልም በየዓመቱ የሚያድስ መድረክ ነው፤ ወጣቱ ከሀገሩ ምርጦች ጎን እንዲሮጥ ዕድል የሚሰጥ፣ ለአዳዲስ አትሌቶች መታያ እና ደማቅ የአደባባይ ስፖርታዊ ሁነት ነው፡፡
እግር ብቻ አይደለም የሚሮጠው፤ መሠረተ ልማትም ይሮጣል
ጀግኖች በችሎታ ብቻ አይፈጠሩም፤ ጠንካራ መሠረትም ይሻሉ። ኢትዮጵያ ዛሬ በስፖርት መሠረተ ልማት ላይ እየሰራች ያለው ስራ ይህንኑ ያረጋግጣል።
ዘመናዊ ስታዲየሞች እየተገነቡና እየታደሱ ነው፤ ባህርዳር በቅርቡ የኢትዮጵያና የሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን ማስተናገዷ ለዚህ ምስክር ነው።
የኮሪደር ልማት የእግረኛ መንገዶችን አስፍቶ፣ ከተሞችን ለሯጭና ለተመላላሽ ወዳጃዊ እያደረገ ነው። ለአትሌቶች የሚሰጠው እውቅናም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።
የዘንድሮው ውድድር በልዩ ድምቀት ነበር የተካሄደው። የክብር እንግዳዋ ኬንያዊቷ ሯጭ ቤያትሪስ ቼቤት ናት፡፡ የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮናዋ ኬንያዊት፣ በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር የዓለም ሪከርድ ባለቤት ናት።
ኢትዮጵያ በአትሌቶቿ ፈጣን እግሮች የዓለም አደባባዮችን ትማርካለች፤ በፈገግታዋ ደግሞ ዓለምን ታስተናግዳለች።
ቡናን ለዓለም ያበረከተችው ኢትዮጵያ፣ የሰው ልጅ መገኛ፣ በአትሌቲክስ የአሸናፊዎች ምድርነቷን የበለጠ የሚያጎላ ነው ታላቁ ሩጫ ውድድር፡፡
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአርባ ምንጭ፣ በሀዋሳ፣ በሐረር፣ እንዲሁም በአፍሪካ ሀገራት ጭምር የሚዘጋጀው ታላቁ ሩጫ በሀገራችን የስፖርት ቱሪዝም መዳበር ቁልፍ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ