Fana: At a Speed of Life!

የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ ልዩነትን በውይይት መፍታትና በትብብር መስራት ይገባል – አቶ ሙሳ አደም

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ ልዩነትን በውይይት መፍታትና በትብብር መስራት ይገባል አሉ የሰላም ሚኒስትር ሙሳ አደም።
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በካሄደው 7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረቡለትን የካቢኔ አባላት ሹመት ያጸደቀ ሲሆን÷ በዚህም አቶ ሙሳ አደም የሰላም ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
ሚኒስትሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት በመሆኑ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።
ሰላም በመንግሥትና ሕዝብ ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፤ ሚኒስቴሩ ቁልፍ ግቦችና ስትራቴጂዎች እንዳሉት አስረድተዋል።
እነዚህን ግቦች ከዳር ለማድረስና ኢትዮጵያ የምትጠይቀውን የሰላም ፍላጎትና መሻት ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
ያለችን አንድ ሀገር በመሆኗ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት በመፍታት በትብብርና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የተጀመረው አካታች የፖለቲካ ልምምድ እና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚከናወነው ሥራ አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።
ለሕዝባችን እና ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ከሰላም ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሁኔታዎች በተቻለን አቅም በትጋት እንሰራለን ብለዋል ሚኒስትሩ።
በትዕግስት ግዛቸው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.