የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነውን ግብርና ለማሳደግ የመስኖ ልማትን ማሻሻል ይገባል – ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነውን የግብርና ዘርፍ ለማሳደግ የመስኖ ልማትን ማሻሻል ይገባል አሉ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር)።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረቡለትን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ሹመት አጽድቋል፡፡
በዚህም ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
ሚኒስትሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ የኢትዮጵያን ከፍተኛ የውሃ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም እና ለማልማት የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጠኝ ከፍተኛ እርጥበት ያላቸውን ጨምሮ 12 ተፋሰሶች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውሃ ሀብት እንዳላት ገልጸው፤ ይህንን ሀብት በአግባቡ በማልማት ሀገርን ለማሳደግ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሻሻልን ጨምሮ በስፋት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነውን የግብርና ዘርፍ ለማሳደግ የዝናብ ውሃ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን የሚፈለገውን ውጤት እንደማያመጣ ጠቅሰው፤ የመስኖ ልማትን ማሻሻል ይገባል ብለዋል።
የገፀ ምድር እና የከርሰ ምድር የውሃ ሀብቶች በአብዛኛው መልክዓምድራዊ አቀማመጣቸው የማይመች እና በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ በመሆናቸው የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን የውሃ ሀብት ተጠቅሞ የወጪ ንግድ ምርትን ለማሳደግ እና የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ የሶላር ኢነርጂን ጭምር መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና፣ ውሃ እና ኢነርጂ ሊለያዩ የማይችሉ የዘርፉ ዋና መሰረቶች እንደሆኑም አመልክተዋል።
በእመቤት ሲሳይ