ካቢኔውን በፍትሃዊነትና አካታችነት ለማደራጀት ጊዜ ተሰጥቶ ተሰርቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱን የመደመር መንግሥት ካቢኔ በፍትሃዊነትና አካታችነት ለማደራጀት ጊዜ ተሰጥቶ ተሰርቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አካሂዷል፡፡
በመደበኛ ስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የካቢኔያቸውን እጩ አባላት ለምክር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን÷ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ሃሳቦችም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው÷ የተሾሙ ሚኒስትሮች የተሰጣቸውን ሃላፊነት በሚገባ መወጣት የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሚኒስትሮችን ሹመት በፍትሃዊነት እና አካታችነት ለማደራጀት ጊዜ ተሰጥቶ መሰራቱን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ሥልጣን ኮፍያ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የትኛውም የተሾመ ሚኒስትር የተሰጠውን ሃላፊነት በሚገባ የማይወጣ ከሆነ በየትኛውም ጊዜ ሊነሳ ይችላል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሮች ሕብረተሰቡን በሚገባ የሚረዱና በፍትሃዊነት አገልጋይ ሊሆኑ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የተሾሙ ሚኒስትሮች ከሌብነትና ብልሹ አሠራር የጸዱ መሆናቸውን ጠቁመው÷ ይህም በተያየ መንገድ መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡
የተሾሙ ሚኒስትሮች የተጣለባቸው አደራ በሚጠበቀው ልክ የማይወጡ ከሆነ ክትትል ተደርጎና ተመዝነው ከሃላፊነት እንደሚነሱ አመልክተዋል፡፡
የተዋቀረው ካቢኔ በጾታ፣ ብሔር፣ እምነት እና ሌሎች መመዘኛዎች ፍትሃዊና አካታች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ