Fana: At a Speed of Life!

እናቅዳለን ፤ ብዙ ሳናስጮህ እንሰራለን ፤ ውጤት ለሕዝባችን እንናገራለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባውን ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ፥ የፋብሪካው መገንባት ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ ወደ ውጭ ልካና ውድ ዋጋ ከፍላ መልሳ የተሰሩ ምርቶችን የምታስገባበትን ሂደት ለማስቀረት ነው ብለዋል ።
ለአብነትም በቡና ንግድ ሂደት ጥሬ ቡና ተወስዶ ውጭ ሃገር ታሽጎና ተቆልቶ በብዙ እጥፍ ተመልሶ የሚገዛውን ውድ ዋጋ አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማዕድን ዘርፍ የሰራነው ስራ ውጤት እያመጣ ነው ብለው ይህንን ፋብሪካ አፋችንን ዘግተን ነው የሰራነው ነው ያሉት።
አክለውም እናቅዳለን ፤ ብዙ ሳናስጮህ እንሰራለን ፤ ውጤት ነው ለሕዝባችን የምንናገረው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ወርቅ ስትልክ ያለማጣሪያ በመሆኑ 30 በመቶ የሚሆነው እንደ ቆሻሻ ተቆጥሮ ይቀነስ ነበር ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ እንደ ብር እና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ውድ ዋጋ ያላቸው ነገሮችም ይጠፉ ነበር ፣አሁን የተገነባው ማጣሪያ ይህንን ችግር የሚቀርፍ እንደሆነ አመልክተዋል።
ፋብሪካውም በዓመት እስከ 80 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ኤክስፖርት ማከናወን የሚያስችል ትልቅ አቅም ያለውና ከአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑት አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በወርቅ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ዘርፎች ጥሬ ዕቃን የማስገባት እና የማውጣት ሂደትን በማስተካከል የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ትልቅ ምዕራፍ ተከፍቷል ነው ያሉት።
በሶስና አለማየሁ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.