ለሠንደቅ ዓላማችን መስዋዕትነት የመክፈል እውነታ በመለዮ ለባሹ በተግባር እየተረጋገጠ ነው – ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሠንደቅ ዓላማችን መስዋዕትነት የመክፈል እውነታ በመለዮ ለባሹ በተግባር እየተረጋገጠ ይገኛል አሉ የፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 19ኛውን ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሐሳብ በዋና መሥሪያ ቤቱ አክብሯል።
በመርሐ ግብሩ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እንዳሉት÷ የፌደራል ፖሊስ አባላት በተሰማሩባቸው ሁሉም አካባቢዎች ሠንደቅ ዓላማው ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የተሰጣቸውን ግዳጅ በጀግንነት፣ በዲሲፕሊንና በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት እየተወጡ ባሉበት ወቅት የሚከበር መሆኑ ልዩ ትርጉም አለው።
ሠንደቅ ዓላማ የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት መገለጫ ከመሆኑም በላይ ለሀገር ሲባል ሕይወትን እስከ መስጠት የሚደርስ መስዋዕትነትን የሚያሳስብ ታላቅ ብሔራዊ ምልክት መሆኑን አስረድተዋል።
ለታላቋ ሀገራችን የሚመጥን፣ በዲሲፕሊንና በሙያዊ ብቃት የታነጸ የፖሊስ ኃይል የመገንባት ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር በጥብቅ የተሳሰረና የሀገራዊ ማንነታችን መገለጫ መሆኑን አንስተው ለሠንደቅ ዓላማው ክብር መስዋዕትነት የመክፈል ዝግጁነት በመለዮ ለባሹ በተግባር እየተረጋገጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ስፍራዎች ተሰማርተው ግዳጃቸውን በጀግንነት እየተወጡ ያሉ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ተግባራቸውን በበለጠ ትጋትና ቁርጠኝነት እንዲያከናውኑ መመሪያ መስጠታቸውንም የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመልክቷል።