የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ፤ ከአህጉራዊ መሪነት እስከ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሰጪነት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ቀን መከበር የሺህ ዓመታት የሉዓላዊነትና የነጻነት ጉዞዋን ወደኋላ መለስ ብሎ ከመቃኘት ባሻገር በጋራ ጥቅም እና በመደመር ፍልስፍና የታደሰውን አዲሱን የዲፕሎማሲ አድማስ የምናበስርበትም ነው።
ሃገራችን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ስኬታማ መንገድ ተጉዛለች፤አሁን ላይም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ ከተሳታፊነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት ሚና ተሸጋግራለች።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ የረጅም ዘመናት ስር ያለው ነው። በጥንቱ የአክሱም ዘመነ መንግሥት ከግሪክ፣ ከሮም፣ ከፋርስ እና ከሩቅ ምስራቅ ሀገራት ጋር የነበረው የንግድ እና የባህል ግንኙነት ኢትዮጵያን በወቅቱ የዓለም ኃያላን ተጽዕኖ ፈጣሪ አድርጓታል።
በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ የዓለም አቀፍ ህጎችና ዲፕሎማሲ በተፈተኑበት ወቅት ሀገራችን ብሔራዊ ሉዓላዊነቷን በመጠበቅ እና ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተስፋ በመሆን በዓለም አቀፍ መድረክ አጽንኦት የሚሰጠው ዐሻራ አኑራለች።
ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታት ማህበር እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) መስራች አባል በመሆን ረገድ የተጫወተችው ሚና፣ እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአፍሪካ ህብረት) ዋና መቀመጫ እንድትሆን ያደረገችው ታሪካዊ ጥረት፣ የአህጉሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል እና የነጻነት ምልክት እንድትሆን አስችሏታል።
ታሪካዊ መሰረቷን የጠበቀው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት፣ በቅርብ ዓመታት ደግሞ በመደመር ፍልስፍና በመቃኘት ወደ አዲስ የመነሳት እና የማንሰራራት ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
ይህ ዲፕሎማሲ ዓለምን በወዳጅ እና በጠላት ከሚከፋፍል አመለካከት ወጥቶ በጋራ ጥቅም፣ በጋራ እሴት እና በባለብዙ ወገን ትብብር ላይ የተመሰረተ ነው።
የመደመር ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያን ከተጽዕኖ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት፣ ከተመልካችነት ወደ ተዋናይነት አሸጋግሯታል።
ኢትዮጵያ የባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት ስብስብ የሆነው የብሪክስ ሙሉ አባል መሆኗ በታሪኳ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስኬት ነው።
በኒው ዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራችን በማዕድን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ያላትን እምቅ አቅም ከዓለም አቀፍ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ እና ገበያ ጋር በማስተሳሰር የጋራ እድገት ለማምጣት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እና በዓለም የንግድ ድርጅት የድርድር መድረኮች ላይ የተደረገው ንቁ ተሳትፎ ሀገራችን በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ያላትን ቦታ በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል።
ከሳውዲ ዓረቢያ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ከቻይና፣ ከሕንድ እና ከሌሎችም ወዳጅ ሀገራት ጋር የተደረጉ ሁለገብ ስምምነቶች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲያድግ፣ የንግድ ልውውጥ እንዲሰፋ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፋጠን ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ቀን በዛሬው ዕለት ጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ.ም እየተከበረ ነው፡፡
ዛሬ የምናከብረው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ቀንም ከጥንቱ የአክሱም ገናናነት እና ከዓለም መንግሥታት መስራችነት ተነስቶ፣ እስከ ዛሬው የብሪክስ አባልነትና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የመጣበትን የትልቅነት መንገድ የምናስብበት ነው።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ጋር በማስተሳሰር፣ ሰላምን በመገንባት፣ የልማት አጋርነትን በማስፋፋት እና የአፍሪካን ድምፅ በዓለም መድረክ ላይ ከፍ አድርጋ በማሰማት ቀጣናዊና አህጉራዊ መሪነቷን በጽኑ መሰረት ላይ እያነጸች ትገኛለች።
በሶስና አለማየሁ