Fana: At a Speed of Life!

የክልሉን ጸጋ ወደ ሀብት በመቀየር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል – አቶ ፍቅሬ አማን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ሀብት በመቀየር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል አሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ፍቅሬ አማን።

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግሥት ቀጣይ ዕቅድን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

‎በመግለጫቸውም÷ ክልሉ በግብርና፤ በቱሪዝም፤ በማዕድንና በሌሎችም ዘርፎች ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብትን የታደለ መሆኑን አንስተው ይህንን ጸጋ ወደ ሀብት በመቀየር የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫ ነው ብለዋል።
‎
የሜካናይዜሽንና የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያለውን ሰፊ አቅም በመጠቀም የአርሶ አደሩን ህይወት በተጨባጭ መለወጥ የሚችሉ ሥራዎች እንደሚሰሩም አንስተዋል።

‎በአርብቶ አደሩ አካባቢ ሰላምን በማጽናትና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በመመለስ የአርብቶ አደሩን ህይወት መለወጥ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ይሰጠዋል ነው ያሉት።

‎ከተሞችን ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝምና ለኑሮ ምቹ ማድረግ ሌላው የመንግሥት ትኩረት መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ በከተሞች የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ ደረጃውን ጠብቆ በስፋት፣ በጥራትና በፍጥነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

‎የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት መጨረስ፣ የመሠረተ ልማት ተደራሽነት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ የክልሉ መንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን በመግለጽ ለዚህም ብቃትንና አካታችነትን መሠረት ያደረገ የአመራር ምደባ መደረጉን ተናግረዋል።
‎
2019 ዓ.ም ለክልሉ የማንሰራራት ዓመት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገርና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት የክልሉ ህዝብ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
‎
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

‎በተስፋየ ምሬሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.