Fana: At a Speed of Life!

ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የልማት ሥራዎች በዘላቂነት ለመደገፍ የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያ ያስፈልጋል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዳጊ ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጧቸውን የልማት ሥራዎች በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችል የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያ ያስፈልጋል አሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፡፡
ኢትዮጵያ በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብስባ ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡
ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከስብሰባው ጎን ለጎን ሀገራት በድህረ ቀውስ ወቅት ማገገም የሚችሉበትን ሁኔታ በተመለከተ በተካሄደው መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮ አቅርበዋል፡፡
የአንድን ሀገር የዕዳ ጫና ማቅለል ለዘላቂ እድገት የመጀመሪያው እርምጃ እንጂ የመጨረሻ ግብ አለመሆኑን ገልጸዋል።
ወቅቱን የጠበቀ የእዳ ጫናን የማቃለል ርምጃዎችና የእፎይታ ጊዜ በመስጠት እንዲሁም የአበዳሪ ተቋማት ትብብርን እውን በማድረግ አዳዲስ ኢንቨስትመንት ለመሳብና ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከዕዳ ጫና ማቅለያዎች ባሻገር በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጧቸውን የልማት ሥራዎች በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችል የፋይናንስ ስርዓትን ገቢራዊ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ ተወዳዳሪና በኢንቨስትመንት የሚመራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ ናት ማለታቸውን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.