የኢትዮጵያ እውነት እና የማርኮ ሩቢዮ ምስክርነት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8 ፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚስትር ማርኮ ሩቢዮ በኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር ድርጊት የሚፈጽሙ ኃይሎች መኖራቸውን እና የኢትዮጵያ መንግሥት ተመጣጣኝ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ተናገሩ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን አስመልክተው በሜሪላንድ አንድሪው የጦር ሰፈር ለጋዜጠኞች በሰጡት ምላሽ÷ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃት የሚፈጽሙ “ተገንጣይ ኃይሎች” መኖራቸውን ጠቅሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ተመጣጣኝ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
አሜሪካ ሽብርተኝነትን እንደማትደግፍ ገልጸው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የሽብር ድርጊት መፈፀማቸውን እና የኢትዮጵያ ምላሽ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም “ተገንጣይ ቡድን” ሲሉ የገለፁት ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን በፌዴራል መንግሥት ላይ ትንኮሳ መፈፀሙን እና የኢትዮጵያ መንግሥትም ሕግ የማስከበር ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተመድ ቻርተር መሰረት አንድ ሀገር የሉዓላዊነት እና የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ሲገጥመው ወይም ጥቃት ሲሰነዘርበት ራሱን ለመከላከል ኃይል የመጠቀም ወይም ወደ ጦርነት የመግባት ሕጋዊነት (Jus ad Bellum) መብት አለው።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የውክልና ጦርነት እያደረጉባት ባሉ የሽብር ድርጊት በሚፈጽሙ ቡድኖች ላይ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያደረገች ሲሆን ይህ ርምጃ በዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲ ሕጋዊ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚስትር ማርኮ ሩቢዮ በኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር ድርጊት የሚፈጽሙ ኃይሎች መኖራቸውን እና የኢትዮጵያ አፀፋ እና የሕግ ማስከበር ዘመቻ ፍትሓዊ መሆኑን መናገራቸው ደግሞ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
በሚኪያስ አየለ