የትግራይ ህዝብን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚያሸጋግረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ህዝብ ከጦርነት ስጋትና ከእርስ በእርስ ግጭት አዙሪት ወጥቶ ወደ አዲስ የሰላምና የልማት ምዕራፍ እንዲሸጋገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ኦ/ር) ያቀረቡት ጥሪ የክልሉን ተስፋ የሚያለመልም ታሪካዊ ሁነት ማብሰሪያ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለመጠይቅ÷ በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የተጎዳውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ለመጠገን እና ህዝቡን ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ ያለመ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ይህ ጥሪ በዋናነት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት መሰረት ያደረገ ሲሆን፤ የትግራይ ህዝብ ከስጋት፣ ከጦርነት አዙሪት እና ከእርስ በእርስ ግጭት ወጥቶ ወደ አዲስ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጎዳና እንዲሸጋገር የሚያስችል ታላቅ የሰላም ማዕቀፍ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ እንዳመላከቱት÷ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚኖረው የትግራይ ተወላጅ ሁሉ እንደ አንድ ህዝብ ወደ ሰላም ማዕድ ሊመጣ ይገባል።
እናቶች ከልጆቻቸው ጋር የሚገናኙበት፣ የተበተኑ ቤተሰቦች የሚሰበሰቡበት እና በጦርነት ምክንያት የተጎዳው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ዳግም የሚነቃቃበት ጊዜ አሁን ነው።
ህዝቡ አንድነቱን እና ሀገራዊ ተቋማቱን መጠበቅ እንዳለበት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በምርጫ ሕጋዊ እና መደበኛ አስተዳደር እስኪመሰረት ድረስ ከፌደራሉ መንግሥት እና ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተለይም የታጠቁ ወጣቶች እንዲሁም ወታደራዊና ፖለቲካዊ መሪዎች ትጥቃቸውን ፈትተው በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ እና ወደ መደበኛ ህይወት እንዲቀላቀሉ የቀረበው ጥሪ÷ በክልሉ የሚገኘውን ወጣት ከእንግልትና ከስቃይ ለማዳን የተወጠነ ትልቅ እድል ነው።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ቁልፍ ይዘቶች የነበሩት ተኩስ ማቆም፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ፣ ትጥቅ መፍታት፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ እና ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እውቅና መስጠት እንደነበሩ ይታወቃል።
የፌደራል መንግሥት በበኩሉ በስምምነቱ መሰረት መፈጸም ያለበትን ኃላፊነት ሁሉ የተወጣ ቢሆንም የጥፋት ኃይሎች ግን ስምምነቱን ወደ ጎን በመተው እና ትጥቅ ከመፍታት ይልቅ ወደ አዲስ መሳሪያ ግዢና አፈሳ በመግባት ሂደቱን ለማስተጓጎል የከሸፈ ሙከራ አድርገዋል።
መንግሥት አሁንም ቢሆን የትግራይ ህዝብ የሰላም እና የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የጸና አቋም ያለው ሲሆን፤ ህዝቡ መሪዎቹን በነጻነት ወደ መምረጥ፣ ወደ እርሻ፣ ወደ ማዕድንና ኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም የትግራይ ከተሞችን ወደ ኮሪዶር ልማት በማምጣት ክልሉን የማደስ ሥራ ላይ ሊረባረብ ይገባል።
ከዚህ ቀደም በነበረው ግጭት በርካታ ወጣቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ እንዲሁም ከፍተኛ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ውድመት ደርሷል። ይህንን ታሪካዊ ስህተት ለማረም የትግራይ ወጣት መሳሪያውን አውርዶ ወደ ሥራው መመለስ እና በመልሶ ግንባታው ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለበት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ህዝብ ጎን በመሆን ለዳግም ግንባታና ለዘላቂ ሰላም ለመስራት ሙሉ ዝግጁነቱን ያረጋገጡ ሲሆን፤ ይህም ለዓመታት ሰላም እና ልማት ለናፈቀው የትግራይ ህዝብ የሚገባው ታላቅ እድል ነው።
በዮናስ ጌትነት