Fana: At a Speed of Life!

የሀሰት ፕሮፓጋንዳን ያከሸፈው የወታደራዊ አታሼዎች ምስክርነት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክና የፖለቲካ ምህዳር በየጊዜው በሚያጋጥሙ ፈተናዎችና የለውጥ ማዕበሎች ውስጥ አልፎ ዛሬ ላለበት ጥንካሬና ጽናት መድረሱ ይታወቃል።

በተለይም የሀገርን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕግ የበላይነትና የሉዓላዊነት አለኝታነቱን በተግባር ያስመሰከረ ዋነኛ የሕዝብ አለኝታ ሆኖ ዘልቋል።

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የውክልና ጦርነት እያደረጉባት ባሉና የሽብር ድርጊት በሚፈጽሙ ቡድኖች ላይ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያደረገች ሲሆን፣ ይህም እርምጃ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሕጋዊ ተቀባይነትን ያገኘ ሆኗል።

ሰሞኑን በቢሾፍቱ አየር ኃይል ለዓለም አቀፍ ወታደራዊ አታሼዎች የተሰጠው ገለጻና ይፋዊ መድረክ የሠራዊቱን ትክክለኛ አቋም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጽ ያሳወቀና ያልተረጋገጡ ወሬዎችን ያጠራ ሁነቶች የተከናወኑበት ሆኖ አልፏል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የልዩ ልዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች በሰጡት ምስክርነት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ደኅንነት ለማስከበርና የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥ ሕግን ተከትሎ የሚወስዳቸው እርምጃዎችና የሚያሳየው የሙያ ብቃት (ፕሮፌሽናሊዝም) ደረጃ በእጅጉ የሚደነቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ የመከላከያ አታሼና የመከላከያ አታሼዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሌተናንት ኮሎኔል ጋሪ ዎልፌንደን፣ ጉብኝቱ ባለፉት ሳምንታት የተከሰቱትን ሁነቶች በሚገባ እንዳብራራላቸው በመጠቆም ሠራዊቱ ሀገሩንና ዜጎቹን ከማንኛውም ሥጋት ለመጠበቅ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የአውስትራሊያ የመከላከያ አታሼ ኮሎኔል ካረን ሳች በበኩላቸው፣ ሠራዊቱ የሀገሪቱን ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር ያደረገውን ጥረት በማድነቅ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ተከባብሮና በሰላም ለመኖር የሁሉም ሀገራት ሉዓላዊነት መከበር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

የሠራዊቱ ዋነኛ ግዴታ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት መጠበቅና የዜጎችን ደኅንነት ማረጋገጥ መሆኑን በመጥቀስ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያደግፉ ያረጋገጡት ደግሞ የጋቦን የመከላከያ አታሼ ኮሎኔል አሪስቲድ አንጊሌት ናቸው።

ከዚሁ ጎን ለጎን የጎረቤት ሀገራት ወታደራዊ ተወካዮች የሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ መረጋጋት የቀጣናው ሰላም መሠረት መሆኑን ያረጋገጠ ነው።

የኬንያ የመከላከያ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ሮባ ዋሪዮ፣ በኢትዮጵያ የሚከሰት የጸጥታ ሁኔታ በኬንያ ላይም ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንዳለው በመጠቆም የመከላከያ ሠራዊቱ ሕግን ተከትሎ የወሰደውን እርምጃ እንደሚረዱ ገልጸዋል።

የደቡብ ሱዳን ምክትል የመከላከያ አታሼ ሌተናንት ኮሎኔል ፖል ቻሙ እና የታንዛኒያ የመከላከያ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ኢያን አልፎንስ ሆሬ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ደኅንነት እየተረጋገጠ መሆኑን መገንዘባቸውንና የኢትዮጵያ ሰላም ለጠቅላላው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።

ይህ የጎረቤት ሀገራት አቋም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያለውን የድንበር ደኅንነትና የጸጥታ ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊሰራጩ የሚችሉ የተሳሳቱ መረጃዎችን በመመከት ረገድ የጎላ ሚና ይጫወታል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚያካሂደው የሰላምና የጸጥታ ማስከበር ሥራ በሕግና በሰብዓዊነት ማዕቀፍ ውስጥ የተቃኘ መሆኑ በዓለም አቀፍ ወታደራዊ አታሼዎች ደረጃ መመስከሩ ደግሞ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጥንካሬ አረጋግጧል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተወካዮች ያሳዩት ድጋፍና የሰጡት አዎንታዊ ምስክርነት በኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት የሚከፍቱና የሽብር ድርጊት የሚያካሂዱ አካላትን ሴራ ባዶ የሚያስቀር ነው።

የኢትዮጵያ ታላቅነትና ጥንካሬ የሚረጋገጠው በሕዝቦቿ አንድነትና በሠራዊቷ ሕግ አክባሪነት ሲሆን፣ ይህ የኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍም ለወደፊቱ ብሩህ ጉዞ እና ዘላቂ መረጋጋት ጠንካራ መሠረት የሚሆን ነው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.