የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2019 ዓ.ም የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዛሬው እለት መካሄድ ጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ምልዓተ ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ ለመቀበልም ሆነ ለመስጠት መታመን መሰረታዊ ነገር መሆኑን አንስተዋል።
ዓለም መታመንን ከቤተክርስቲያን ሰዎች ትጠብቃለች ብለዋል።
ጉባኤውም በቤተክርስቲያን መታመን እንዲኖር አብዝቶ የመስራት እና የማሰራት ግዴታና መለኮታዊ ኃላፊነት አለበት ነው ያሉት፡፡
የሀብት አጠቃቀም፣ የምዕመናን አያያዛችን፣ ሀዋርያዊ ተልዕኳችን ዘመኑን የማይመጥን በማለት ገልጸው÷ የቤተክርስቲያን መሪዎች እና ምዕምኑ የተሳሳተ ሲኖር ለማስተካከል እና የተዛባን ለማቃናት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በጉባኤው የአሰራር ክፍተቶቻችንን በሚገባ ፈትሸን ዘላቂ መፍትሔን በማስቀመጥ በሀገር ውስጥና በውጭ አህጉረ ስብከት ያሉ እድሎችን በታቀደና በተጠናከረ ሁኔታ መስራት የሚቻልባቸውን እድሎች መፈተሽ አለብን ብለዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተልዕኮ መወጣት የሚችለው ሀገር ሰላም ሲሆን መሆኑን ጠቁመው፤ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ከመፀለይ ባለፈ የማግባባት እና የማስታረቅ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ ለሀገር ሰላም ቅዱስ ሲኖዶስ ሊኖረው የሚችለውን ሚና በተመለከተ ውይይት እንደሚደረግ እና ሰላም እንዲሰፍን ለባለድርሻ አካላት ሲኖዶሱ የሰላም ጥሪ እንደሚያስተላልፍ ጠቁመዋል፡፡
በቅድስት አባተ