Fana: At a Speed of Life!

ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን በማሳደግ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እየተሰራ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ተደራሽና ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን በማሳደግ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እየተሰራ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሠረታዊ የዕለት ተዕለት ፍጆታዎችና በቤት ኪራይ ላይ እየታዩ ያሉ ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመቆጣጠር እንዲሁም የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል የሚያስችሉ ዘለቄታዊና የአጭር ጊዜ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡
ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በነበረ ውይይት በተለይም በሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ የዳቦ፣ የታሸገ ውሃና የቤት ኪራይ ዋጋዎች ላይ የሚታዩ ያልተገቡ ጭማሪዎች ላይ ዝርዝር ግምገማ እንደተካሄደ አንስተዋል።
የምርት አቅርቦትን ማሳደግ፣ የገበያ ማዕከላትን ማስፋፋትና የደላላ ሰንሰለትን ማሳጠር፤ የሸማቾች ማኅበራትን ማጠናከር፤ የእሑድ ገበያዎችን ማስፋፋት፤ ቁጥጥርንና የሕግ ማስከበርን ማጠናከር እና የቤት ኪራይን በተመለከተ የአከራይና የተከራይ ግንኙነት በሕግ፣ በውል ስምምነትና በጋራ ኃላፊነት መመራትን የመሰሉ ርምጃዎች በመወሰድ ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
ከባለድርሻ ጋር በተደረገው ውይይት የአቅርቦት ችግሮችን ከመሠረቱ በመፍታት፣ ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን በማረጋገጥና ሕገወጥ የዋጋ ጭማሪዎችን በመቆጣጠር የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ጠቁመዋል።
ሕብረተሰቡ አስተዳደሩ ባመቻቻቸው የሸማቾች ማኅበራትና የእሑድ ገበያዎች በመገበያየት የኑሮ ወጪውን እንዲቀንስ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ዜጎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ወይም የገበያ ሕግ ጥሰት ሲያጋጥማቸው በቂ ማስረጃ በማቅረብ ለሚመለከተው የከተማ አስተዳደር አካል ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ ከተረጋገጠ መረጃ ውጭ ወሬዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን በጋራ መደገፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.