Fana: At a Speed of Life!

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የELMIS ፕሮጀክት ላይ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ የሙስና ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩት ላይ ክስ ተመሠረተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠረውን የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ የነበረው ብርሀኑ አለቃ አስገዶም እና በግብረ አበሮቹ ክስ ተመስርቷል።
ፌደራል ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ከሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሂድ የቆየውን ጥልቅ ምርመራ በማጠናቀቅ ነው ለፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በመላክ ክስ የተመሰረተው።
ብርሃኑ አለቃ አስግዶም እና ሌሎች የተቋሙ ሠራተኞች፣ የሠራተኛና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲ ባለቤቶች እና ሌሎች ግለሰቦችን ጨምሮ 13 ሰዎች በዚህ ወንጀል ውስጥ የመሳተፋቸውን እና ተጠርጣሪዎቹ የተሰጣቸውን የመንግሥት ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እና ፕሮጀክቱን ከአሠራር ውጭ በማንቀሳቀስ ከጅምሩ የሲስተሙ የጥራት ደረጃ በተገቢው ሳይረጋገጥ ሥራ እንዲጀምር ማድረጋቸውን ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል።
ብርሃኑ አለቃ አስግዶም ላልተማሩ ወይም በቂ ሥልጠና ላልወሰዱ ለ81 ሺህ 236 ግለሰቦች የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሠራተኛ ላልሆኑና ተቋሙ ከማያውቃቸው ሦስት ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ልዩ የሲስተም አስተዳዳሪ መብት በመስጠት ዜጎች ያልሰለጠኑበትን ሐሰተኛ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኙ ማድረጉን በምርመራ እንደተደረሰበት ተመላክቷል።
ለዚህ የወንጀል ድርጊት ሁለት ሐሰተኛ የባንክ ሒሳብ ደብተሮች እንዲከፈቱ በማድረግ በዚህ ሕገወጥ መንገድ አጠቃላይ 1 ቢሊየን 13 ሚሊየን 609 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡም በምርመራ ተረጋግጧል።
በተጨማሪም የወንጀሉ ፍሬ የሆነ በባንክ ሂሳብ ውስጥ ይገኝ የነበረ 249 ሚሊየን ብር የታገደ ሲሆን ወንጀለኞቹ በረቀቀ ዘዴ ገንዘቡን ወደ የክሪፕቶከረንሲ በመቀየር ያስቀመጡትን 965 ሺህ 508 ዶላር ከፍተኛ ጥበብ በተሞላበትና በቴክኖሎጂ በታገዘ ምርመራ በፍርድ ቤት በማሳገድ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ የውጭ ምንዛሪ ሳያስገቡ የታገዱ ኤጀንሲዎችን እግድ ያለአግባብ በማንሳት 10 ሚሊዮን 100 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበሉ እና 64 ሺህ 500 ዜጎችን በሐሰተኛ ቪዛ ሰነድ ወደ ጆርዳን እና ወደ ሌሎች የዓረብ ሀገራት በመላክ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን ፖሊስ ባደረገው የተጠናከረ ምርመራ ማረጋገጡን ገልጿል።
ፌደራል ፖሊስ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ከፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል እና ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ምርመራ በተጠርጣሪው ስም በለሚ ኩራ፣ በቦሌ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች የተገዙ ከ55 ሚሊየን እስከ 68 ሚሊየን ብር የሚያወጡ 6 ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም በ68 ሚሊዮን ብር የተገዛ አንድ V6 ዘመናዊ መኪና በኤግዚቢትነት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርጓል።
እንዲሁም በዚህ ወንጀል ውስጥ የተሳተፉ እና ሕጋዊነትን ሽፋን በማድረግ መንግሥት ማግኘት የነበረበትን የውጭ ምንዛሪ ሳያስገቡ በቀሩ ኤጀንሲዎች ላይ እያደረገ ያለውን ምርመራ አጠናክሮ መቀጠሉን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ልጆቻቸው ወደ ውጭ ሀገር ሄደው መዳረሻቸው የጠፋባቸው ቤተሰቦች እና ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ መረጃ ያላቸው ዜጎችም በዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፣ በነፃ የስልክ መስመር (991) እና በሰው አልባ ስማርት ፖሊስ ጣቢያ (SPS) አማካኝነት ጥቆማ እንዲሁም በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በአካል በመቅረብ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.