የመገጭ ግድብ ለጎንደር ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ይዞ የመጣ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመገጭ ግድብ ለጎንደር ከተማና በዙሪያዋ ላሉ ከተሞች ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ይዞ የመጣ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ በዛሬው ዕለት ለታሪካዊቷ ጎንደር እና ለአካባቢዋ ማህበረሰብ ትልቅ የምስራች የሆነውን የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት በይፋ መርቀን ለአገልግሎት አብቅተናል።
ይህ ፕሮጀክት ረጅም ዓመታት የዕቅድና አተገባበር መጓተት ቢፈታተነውም፣ በመደመር እሳቤ የአፈጻጸም ችግሮቹን በመፍታት ወደ ታላቅ በረከት መለወጥ ችለናል ብለዋል።
ግድቡ 185 ሚሊየን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለውና ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በመስኖ በማልማት በአካባቢው የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ በማድረግ የአካባቢውን ነዋሪዎች የልማት ጥያቄ በዘላቂነት መመለስ የሚያስችል ታላቅ ፕሮጀክት እንደሆነም አስረድተዋል።
ግድቡ ለጎንደር ከተማና በዙሪያዋ ላሉ ከተሞች አስተማማኝ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ከማቅረብ ባለፈ፣ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ይዞ የመጣ መሆኑንም አንስተዋል።
በግድቡ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ዙሪያ የሚስፋፉት የከተማ ግብርና፣ መጠነ ሰፊ የዓሳ እርባታ፣ እንዲሁም ለቱሪዝም ልማት የሚሆኑ የመዝናኛ ሪዞርቶች እና ሎጆች ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩና የንግድ እንቅስቃሴውን እንደሚያሳድጉ ገልጸዋል።
ይህን ስኬት ለዕይታ ለማብቃት በጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እውን ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
አክለውም ጎንደር ገና ብዙ ሊሰራላት የሚገባ ከተማ እንደመሆኗ ህዝቡ በልማቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ እድገት ሁሉንም አካባቢዎች ያካተተና ሁሉንም ዜጋ እኩል የሚያቅፍ እንዲሆን በትጋት መስራታችንን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።