ኢትዮጵያ ምርታማነትንና የኃይል ዋስትናን የሚያረጋግጠውን “NEP 3.0” ፕሮግራም ይፋ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ሦስተኛው የውኃና ኢነርጂ ሳምንት ላይ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም “NEP 3.0” ይፋ ተደርጓል።
በውኃና ኢነርጂ ሳምንት መርሐ ግብር ላይ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍና ከሀገር ውስጥ አጋሮች ጋር በመተባበር “ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም 3.0 (NEP 3.0)” በይፋ አስተዋውቋል።
በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ዳቢ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አዲሱ ፕሮግራም የሀገሪቱን የኃይል ዘርፍ አካሄድ ከመሠረቱ የሚቀይር አዲስ ምዕራፍ ነው።
ፕሮግራሙ ከዚህ ቀደም የነበረውን “መስመርና ቆጣሪ የመዘርጋት” ትኩረት በመቀየር፣ ኤሌክትሪክን በቀጥታ ከምርታማነት፣ ከኢኮኖሚ ዕድገት እና ከዜጎች ማኅበራዊ ሕይወት ጋር ማጣመር ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የኤሌክትሪክ ኃይልን ከግብርና ማቀናበሪያዎች፣ ከመስኖ፣ ከእህል ወፍጮዎች፣ ከዶሮ እርባታ፣ ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች እና ከዲጂታል መዋቅር ጋር በጥብቅ እንደሚያያዝ ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ የሚመነጨው የኃይል መጠን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ ተመጣጣኝና አስተማማኝ ኃይል ለአባወራዎች፣ ለአርሶ አደሮች፣ ለትምህርት ቤቶችና ለጤና ተቋማት ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ስማርት ሜትሪንግ ቴክኖሎጂን በመዘርጋትና የታሪፍ ማሻሻያ በማድረግ የማስተላለፍና ማከፋፈል የኃይል ብክነትን መቀነስ፣ እንዲሁም በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሥር በመረጃ የተደገፈ ዕቅድ የሚመራ ብሔራዊ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር መዋቅር መዘርጋት ዋና ተግባሩ መሆኑን አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በመንግሥትና በግል ዘርፍ አጋርነት አማካኝነት ከዋናው መስመር ውጭ ያሉ አነስተኛ የፀሐይ ኃይል አውታሮችን ማስፋፋት ሌላኛው ዋና ተግባር ነው ማለታቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።