Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ባለፉት 3 ወራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል – ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት ክልሉ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት ነው፡፡
በክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት በግብርና፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና የክልሉን የመልማት አቅም በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም የማዕድን ዘርፉን ለማልማት በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸው በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 3 ሺህ 833 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን ጠቅሰዋል።
ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን እና አምራቾች ሕጋዊ መንገድን በመከተል ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ይጠናከራል ነው ያሉት።
እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ የበጋ መስኖ ልማትን በማጠናከር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ተግባራት እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።
በገቢ አሰባሰብ ዘርፍ የታየውን መነቃቃት በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብር አሰባሰብ ሂደትን በመከተል የገቢ አቅምን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ማሳሰባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
እንዲሁም በአምስት ሚሊየን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ የወጣቶችን ተሳትፎ ማጎልበት፣ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስፋፋትና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚኖረውን ድርሻ ማጠናከር እንደሚጠበቅ ተናግረው በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን የማስቀጠል ተግባር ይጠናከራል ብለዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.