የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) “መደመር” መጽሐፍ ወደ ሩስኪ ተተርጉሞ ለንባብ በቃ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “መደመር” መጽሐፍ ወደ ሩስያ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ በቅቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ፥ በሩሲያ የተዘጋጀውን የመጽሐፉ የምረቃ መርሃ ግብር ተገኝተው በመካፈላቸው ታላቅ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህ ታሪካዊ ስኬት የመደመር ፍልስፍና ከኢትዮጵያ ሀገር በቀል እውቀት ተነስቶ ዛሬ ላይ ድንበር በመሻገር ወደ መላው ዓለም እየሰፋ መሄዱን የሚያሳይ ህያው ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
“መደመር” መጽሐፍ ከዚህ ቀደም ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ በእንግሊዝኛ፣ በቻይንኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለብዙኃን አንባቢያን መድረሱን አስታውሰዋል።
አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሀሳብ ድንበር ተሻግሮ በሰፊው የሩሲያኛ ተናጋሪ ደጃፍ መድረሱ የፍልስፍናውን ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነትና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ይበልጥ ያጎለብተዋል ሲሉ አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሩሲያ ለብዙ ኢትዮጵያውያን የሥነ ጽሑፍና የዕውቀት መማሪያ ምድር ሆና እንዳገለገለች ሁሉ፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሀሳብ በሩሲያኛ ቋንቋ ለሩሲያ አንባቢያን መድረሱ የዕውቀት ልውውጡን ሙሉ ያደርገዋል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ስኬት መሳካትና ለመጽሐፉ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የሩሲያ ቱዴይ (RT) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና አመራሮች ያደረጉትን ጥረትና ትጋት አድንቀዋል።
ይህ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የኢትዮጵያን የበለጸጉ ሀገር በቀል እውቀቶች፣ ባህሎችና ፍልስፍናዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ይበልጥ ለማስተዋወቅና በሕዝቦች መካከል ጠንካራ የባህልና የሃሳብ ድልድይ ለመገንባት እጅግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።