ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሻል ያለውን ቴክኖሎጂ መታጠቅ ችላለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሻል ያለውን ቴክኖሎጂ መታጠቅ ችላለች አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን የሱ-35 የጦር ጄቶች ከሩሲያ በተረከበችበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሚቀጥሉት ዓመታት በብዙ መልኩ የኢትዮጵያ ራሷን የመከላከል አቅሟን ትገነባለች ብለዋል።
እንደ ከዚህ ቀደሙ በልመናና በችሮታ የምንጎናጸፈው የሉዓላዊነት ጉዳይ አይኖርም ሲሉም አረጋግጠዋል።
ትልቅ፣ ታሪካዊ እና ከ130 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያለን ሀገር ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚያው ልክ አቅም መገንባት ካልቻልን በስተቀር ትልቁም ትንሹም ሊሳሳት ይችላል በማለት ገልጸዋል።
ስለዚህ ራሳችንን ለመከላከል፣ እንደ ሀገር ለመቆየት እና ለልጆቻችን ሀገር ለማጽናት ዝግጅት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ኮንትራቱ ጊዜው ሳይደርስ ቀደም ብሎ ርክክብ መፈጸሙ ትልቅ ድጋፍ መሆኑን ገልጸው፤ ኤስ 400 ስንረከብ እና ሱ35 በተሟላ አቅም ወደ ስራ ሲገባ ክሩዝ እና ባለስቲክ ሚሳኤልም የማክሸፍ አቅማችን በከፍተኛ ደረጃ ያድጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የማጥቃት ብቻ ሳይሆን የመከላከል አቅሟን በጣም ማሳደግ እንዳለባት ጠቅሰው፤ በቀጣይ አጠቃላይ ብቃቷ የሚገለጽበት ጊዜ እንደሚመጣ ተናግረዋል።
ቀድሞ መናገር ሳይሆን ሰርቶ ጨርሶ ማሳየት በሚለው መርህ ዛሬ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሻል ያለውን ቴክኖሎጂ መታጠቅ የቻለች ሀገር መሆን ችላለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ክልል ከጥቃት የተጠበቀ እንዲሆን ለሚፈልጉ ዜጎች የደስታ ቀን መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን አቅም በቀጣይነት በመገንባት የኮራች፣ የጸናች ለልጆቿ የምትሸጋገር ኢትዮጵያን ለማኖር እንደ መሰረት የምንጠቀምበት ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል።