ታላቅ ሃገር ነን፣ ታሪካዊ ሃገር ነን፤ በዚያው ልክ አቅም መገንባትና ዝግጅት ያስፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቅ ሃገር ነን፣ ታሪካዊ ሃገር ነን፤ በዚያው ልክ አቅም መገንባትና ዝግጅት ያስፈልጋል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመጀመሪያዎቹን 12 የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች ከሩሲያ በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በብዙ ጠላት የተከበበች ሀገር ናት፣ ልጆቻችን ሀገር እንዲኖራቸው፣ የአየር ክልላችን እንዳይደፈር በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት አጠቃላይ የኢትዮጵያን ስጋት ለመቀነስ እንዲሁም በዓለም ሀገራት ዘንድ የአየር የበላይነትን ለመውስደ የሚደረገውን ሩጫ በመገንዘብ ከሩሲያ መንግሥት ጋር የሱ-35 4ኛ ትውልድ ኤር ክራፍት ስምምነት መፈጽሙን አብራርተዋል፡፡
ስምምነቱ ጊዜው ደርሶ የመጀሪያው ዴሊቨሪ ስምምነት በ2027 ቢሆንም ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በህንድ በነበረን ቆይታ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያቀርቡልን ባቀረብነው መሰረት የመጀመሪያውን ሱ-35 ተረክበናል ብለዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር 12 የሱ ሶስት ኤርክራፍቶችን እንዲሁም አራት ኤስ 400 የአየር መከላከያ ስርዓቶችን ትረከባለች፣ እነዚህ አቅሞች ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም አላቸው ነው ያሉት፡፡
በተለያዩ ሀገራት በግጭት ጊዜ ያለው ምስቅልቅል ችግር ከመፈጠሩ በፊት በሰላሙ ጊዜ መደረግ የሚገባውን ዝግጅት ካለማድረግ የሚመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ የምናየው የሱ 35 ኤር ክራፍት በዓለም ላይ ምርጡ የሚባለው የዘመኑን ቴክኖሎጂ የታጠቀ ኤር ክራፍት ነው ያሉ ሲሆን፤ የአየር እና የምድር ውጊያዎችን ማድረግ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም የክሩዝ ሚሳኤሎችን የማክሸፍ አቅም ያለው ጄት መሆኑን ጠቅሰው፤ ክሩዝ ሚሳኤሎችን እስከ 200 ኪሎ ሜትር ድረስ መነሻቸውን በማጥናት ማምከን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
ይህን የአየር መከላከል አቅም ካልገነባን እንደ ሀገር ህልውናችንን ለማስቀጠል እንቸገራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ምክንያት ሰው ስናሰለጥን ቆይተናል፤ አሁን የታጠቅናቸው ሱ-35ቶች በበቂ ሁኔታ የኢትዮጵያን የአየር ክልሎች ለመከላከል ያግዛሉ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በቂ የጦር አቅም ያላቸው ሀገራት በቀላሉ አይደፈሩም፤ ያልተዘጋጀ መንግሥት ውጊያን ይጋብዛል፤ የተዘጋጀ ግን ውጊያን ያስቀራል፤ ከዚህ አንፃር የዛሬው ስምምነት ከፍተኛ ትርጉም አለው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሰብ ሰሃራ አፍሪካ ኢትዮጵያ የሱ- 35 የታጠቀች ብቸኛዋ ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ በድሮን ብቻ ሳይሆን በሱ 34 እና 35 የአየር የበላይነቷን እያረጋገጠች ትገኛለች ብለዋል፡፡