ልዩ የአየር ላይ የማጥቃት ጥበብ የተላበሰው ሱ 35 4++
ፑጎቼቪስ ኮብራ የተሰኘውን የማጥቃት ልዩ አቅም አየር ላይ የሚያስመለክተው ሱ 35 4++
በዛሬው ዕለት የዓለምን ቀልብ የሳበ የበርካቶችን ትኩረት የሰረቀ መረጃ ከሞስኮ ሰማይ ስር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ 12 የሱ 35 የጦር ጄቶችን በይፋ ወደ አየር ኃይሏ ቀላቅላለች፡፡
በዓለም ላይ በወደር የለሽነቱ የሚነገርለት የሩሲያው ሱ 35 ምን የተለዩ ነገሮችን ይዟል የሚለው ደግሞ ሌላኛው የበርካቶችን ቀልብ የሳበ የኢትዮጵያውያንን ልብ የሚያሞቅ ሆኗል፡፡
በሁለት ሞተሮቹ አየር ላይ ሲበር እስከ 60 ሺህ የጫማ ከፍታ ላይ በሰዓታት እስከ 2ሺህ 400 ኪሎ ሜትሮችን መወንጨፍ የሚችል አቅም ያለው ነው፡፡
ይህም በየትኛውም አይነት የአየር ሁኔታና መልክ ዓምድር ላይ የአየር የበላይነትን መቆናጠጥ የሚያስችለውን አቅም ፈጥሮለታል፡፡
ይህንን የጦር ጄት የሚዘውሩ አብራሪዎች ከቴክኖሎጂ ጋር ለጠላት ፈተና የሚሆኑ በ3ዲ የታገዘ የውግያ አቅምን የተላበሱ ያደርጋቸዋል፡፡
የአየር ላይ ታርጌቶቹን ከ350 እስከ 400 ኪሎ ሜትሮች ውስጥ የመለየት አቅም የተፈጠረለት በተሞከረባቸው አካባቢዎች ሁሉ ጠላትን በታሰበለት፣ በታቀደለትና በተመጠነለት ወሰን ውስጥ ድባቅ መቶ ያሳየ ነው፡፡
ከረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች እስከ ልዩ ተልዕኮ ተሸካሚ ፈንጆች ድረስ በመያዝ የትኛውንም ተልዕኮ መወጣት የሚችል አቅም አለው፡፡
በርካቶቹ የጦር ጠበብቶች ፑጎቼቪስ ኮብራ የተሰኘውን የማጥቃት ልዩ አቅም አየር ላይ የሚያስመለክተው ይሁ ሱ35 የጦር ጄት መሆኑን በልዩነት ይመሰክሩለታል፡፡
አየር ላይ እየተከላከሉ ማጥቃትን የተካነውን ሱ35 የ4ኛው ትውልድ የጦር ጄት ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት በይፋ ታጥቃለች። በዚህም ከሰሀራ በታች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር በመሆን ጠንካራ ክንዷን ለዓለም ገልጣለች፡፡
ይህም በቅርቡ የ5ኛው ትውልድ የአየር ኃይል አቅምን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ የማፋጠን ጥረት አንዱ ማሳያ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያን በቀጣናውና በአህጉሪቱ ታፍራና ተከብራ የምትኖር ሀገር ለማድረግ የተያዘው ውጥን እየተፋጠነ ስለመሆኑ ይህም አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በአሸናፊ ሽብሩ