የአባይ ተፋሰስን በተቀናጀ መንገድ ማልማት የኢትዮጵያን የኃይል ደህንነት ለማጠናከር ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአባይ ተፋሰስን በተቀናጀ መንገድ ማልማት የኢትዮጵያን የኃይል ደህንነት ለማጠናከር ወሳኝ ነው አለ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፡፡
በ3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የቀረበው ጥናት የአባይ ተፋሰስ ለውሃ፣ ለኃይልና ለምግብ ዋስትና በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ጥናቱን ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሊክ ምህንድስና ተባባሪ አሰግድ ጋሻው (ፕ/ር) የአባይ ተፋሰስ ሰፊ የውሃና የመሬት ሀብት ቢኖረውም ሀብቱን በተቀናጀ መንገድ በማልማት የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
የአባይ ተፋሰስ በአካላዊ ሁኔታ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር የሚደርስ የመስኖ ልማት አቅም እንዳለው ቢገመትም በኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ደረጃ ሊለማ የሚችለው አካባቢ 815 ሺህ ሄክታር ገደማ እንደሆነ ተመላክቷል።
ይህንን የመስኖ ልማት ለማስፋፋትም በዓመት 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ያህል ውሃ ሊያስፈልግ እንደሚችል ነው የተገለጸው፡፡
በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙ የውሃ ማከማቻ ግድቦችን በተቀናጀ ሁኔታ በማልማትና በማስተዳደር ኃይል የማመንጨት አቅምን የበለጠ ማሳደግ እንደሚቻል ተጠቁሟል።
በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከሌሎች ግድቦች ጋር በማቀናጀት የውሃ ፍሰትን መቆጣጠር፣ በደረቅ ወቅት የኃይል ምርትን ማረጋጋትና የኤሌክትሪክ አቅርቦትን የበለጠ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
የግድቦችን አሠራር በጋራ ማስተዳደር፣ የልማት ፕሮጀክቶችን በደረጃ ማስፈጸም፣ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙ የውሃ፣ የኃይልና የግብርና ልማቶችን በተቀናጀ አሠራር ማስተሳሰር እንዲሁም የውሃ ሀብት አጠቃቀምን ለመወሰን የሚረዱ ዘመናዊ የውሳኔ ድጋፍ ሥርዓቶችን መጠቀም ከተጠቆሙት የመፍትሔ አቅጣጫዎች መካከል ይገኙበታል።
የአባይ ተፋሰስን በተቀናጀ የግድቦች ልማት፣ በውሃ ማከማቻና በመስኖ ልማት በማስፋፋት የኃይል ምርትን ለማሳደግ፣ የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻልና የውሃ ሀብትን በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም ከፍተኛ አቅም አለው፡፡
በአጠቃላይ የአባይ ተፋሰስን በሁለገብና በተቀናጀ መንገድ ማልማት የኢትዮጵያን የኃይል ደህንነት ለማጠናከር፣ የመስኖ ግብርናን ለማስፋፋት፣ የምግብ ዋስትናን ለማሻሻልና ክልላዊ የኃይል ትስስርን ለማጎልበት ወሳኝ አቅም እንዳለው ተመላክቷል፡፡