የሰማዩ ዐርበኛ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንድ የፈረንሳይ ስሪት «ፖቴዝ 25» አውሮፕላንና በጥቂት አብራሪዎች ሥራውን የጀመረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነትና ከዚያም በኋላ በደርግ ዘመን በሶቪየት ኅብረት ስሪት አውሮፕላኖች እያደገ መጥቷል።
አየር ኃይሉ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ውስጥ ገጥመውት የነበሩትን የተቋም ግንባታ ድክመቶች በመቅረፍ፣ የመደመር መንግሥት በወሰደው ርምጃ ባለፉት አምስት ዓመታት የ85 ዓመቱን ሥራ የሚተካከል ግዙፍ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል እመርታ አስመዝግቧል።
በአሁኑ ወቅት ትጥቁን በሱ 35 አውሮፕላኖች አዘምኖ የሰለጠነ ሰብአዊ አቅምና ዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በማቀናጀት የቀጣናው ወሳኝ ተቋም መሆን ችሏል።
የአየር ኃይልን ሚና ከሰማያዊ ከፍታ አንፃር ለመረዳት የታዋቂው ፈረንሳዊ ደራሲና አብራሪ አንቷዋን ደ ሴንት-ኤክዙፔሪ ‘Wind, Sand and Stars’ በተሰኘው መጽሐፉ፤ አውሮፕላን የውጊያ መሣሪያ ብቻ አይደለም፤ የመሻት እና የነፃነት መሣሪያ እንጂ። በሰማይ ላይ ስትሆን ምድርንና የሰውን ልጅ እውነተኛ እሴት በላቀ ከፍታ ላይ ታየዋለህ ይላል።
ይህ ፍልስፍና አየር ኃይል ከተራ ውጊያ የዘለለ፣ ሀገራዊ ነፃነትን ከሰማይ ከፍታ ልቆ የሚያረጋግጥ የአየር ላይ የነፃነት ዓምድ መሆኑን ያስገነዝባል።
ከፍ ብሎ መብረር የሞራል ከፍታም አለው። የፍሬድሪክ ኒቼ ‘Thus Spoke Zarathustra’ በዘይቤያዊ ሐሳቡ፥ በከፍታ ላይ መኖርን፣ እንደ ንስር መብረርን እና ከአሮጌው የሞራል ዕሴት ነጻ መውጣትን ያነሳል።
ከፍ ብሎ የሚበር ሰው በምድር ላይ ያሉትን ትናንሽ ግጭቶችና ጭንቀቶች ንቆ፣ ግን ደግሞ አርቆ ማየት እንደሚችል ይገልጣል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በፈረንጆቹ 2030 ከአፍሪካ ቀዳሚና ግዙፍ የመሆን ራዕይ ሰንቆ ከፍ ብሎ ለመገኘት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ለዚህ ስኬትም አሁን ያለውን የጦር አውሮፕላኖች እና የተዋጊዎች ቁጥር በእጥፍ ደረጃ ለማሳደግ፣ ቴክኖሎጂውንም ከአራተኛው ትውልድ ቀስ በቀስ ወደ አምስተኛው ትውልድ ለማሸጋገር ግልጽ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማብሠራቸው ይታወሳል።
ይህ ታሪካዊ ስኬት እና የቀጣይ ዘመን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የደህንነት መዋቅር ከፍ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ሀገራችንን ከማንኛውም ጥቃት ሙሉ በሙሉ ለመጠበቅ የሚያስችል የማይናወጥ ወታደራዊ አቅም እውን አድርጓል።
በአጠቃላይ አየር ኃይላችን በቀጣናው ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም ጥቃቶች ለማምከን እና ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ቁመና በመገንባት አስተማማኝ ጋሻና መከታ፣ የነፃነታችን እና የሉዓላዊነታቸን ዓርማ ሆኖ የኢትዮጵያን ከፍታ ያረጋግጣል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በአሰፋ አሕመድ