Fana: At a Speed of Life!

“የጥቅምት እሸት አወደ…”

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት ማኅበራዊ ሕግና የሕይወት ፍልስፍና ብቻ ሳይሆን፣ ባህልን፣ ተፈጥሮንና የሴቶችን ሚና የሚያገናኝ የማንነት ምሰሶ ነው።
በዚህ የባህል ዓለም ውስጥ አቴቴ የእምነትና የጸሎት ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የሴቶች ድምፅ፣ የማኅበረሰብ አንድነትና የተፈጥሮ ምስጢር መገለጫ ሆና ትታያለች።
የክረምቱ ጨለማ አልፎ በጸደይ ብርሃን መተካቱን ተከትሎ በአብዛኛው በመስከረም መጨረሻ እና በወርሃ ጥቅምት የምትከበር በዓል ናት – አቴቴ።
በዓሉንም ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን በ1962 ዓ.ም. ባሌ ጎባ ላይ በጻፈው “አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ” ግጥም እንዘክረው። ኪናዊ ሥራውንም የልጅነት ትዝታ፣ የጠፋ ማንነትና ዘመናዊነት በሚሉ እዶች ውስጥ እንየው።
የልጅነት ትዝታ…
የባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን “አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ” ግጥም ወደ አንድ የተረሳ የልጅነት ዓለም የሚወስድ የትዝታ ጉዞ ነው።
“አቴቴ” በኦሮሞ ባህል የሴቶች መንፈሳዊና ማህበራዊ ሥርዓት ብቻ ሳትሆን፣ በገጣሚው አዕምሮ የተቀረጸች የልጅነት ዓለም ምልክት ትሆናለች።
“አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ
እጄን በትዝታሽ ያዢኝ
በሕልም ጣቶችሽ ሳቢኝ”
ሲል ገጣሚው የሚጠራት አቴቴ በእውን የምትገኝ አይደለችም፤ በትዝታ ብቻ የምትሳል የልጅነት ዓለም ናት። ይህም ግጥሙን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በናፍቆት ስሜት ያጠምቀዋል።
ይህ ትዝታ ግን በተፈጥሮና በገጠር ሕይወት ምስሎች ይበልጥ ሕያው ይሆናል። “የጥቅምት እሸት” የሚለው ምስል፣ ከ“እሳት ዳር ተረት” እና ከአውድማው እንቅስቃሴ ጋር ሲጣመር፣ የልጅነትን ዓለም በዓይን ብቻ ሳይሆን በሽታ፣ በድምፅና በእንቅስቃሴ እንዲደርሰን ያደርገናል።
“ተግ ሲል ያንቺ ሽውታ” እና “የጥቅምት እሸት አወደን” የሚሉት ስንኞች ትዝታን በሽታ የሚያስቃኙ ስሜታዊ ምስሎች ይፈጥራሉ። ከዚያም “አውድማው”፣ “ሰንበሌጥ”፣ “ሰብል”፣ ግጦሽና እንስሳት የተሞላው ዓለም ይመጣል። እዚህ ገጣሚው የሚያስታውሰው የግል ልጅነት ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ፣ ከሥራና ከማህበረሰብ ጋር የተሳሰረ የባህል ሕይወትን ነው።
የጠፋ ማንነት…
የግጥሙ ናፍቆት ስር የሚሰደው የልጅነት ዓለም ብቻ ስለነበረ አይደለም፤ ያ ዓለም ከገጣሚው ርቆ ስለጠፋ ነው። እዚህ ላይ የጠፋ ማንነት ጉዳይ ይገጥመናል።
“የኔ እጅ እኮ እርፍ አይጨብጥም
የኔ ክንድ ተልም አይተልምም
የኔ ጣት አረም አይነቅልም”
የሚሉት ስንኞች በጣም ጠንካራ የሆነ ተቃርኖ ይፈጥራሉ።
እጅ፣ ክንድና ጣት የሥራና የገጠር ሕይወት ምልክቶች ሲሆኑ፣ እሱ ግን ከእነዚህ ሥራዎች ተለይቷል። የቀረው “በፊደል መፈደል” ብቻ ነው።
በዚህ የቃላት ተቃርኖ ገጣሚው የተማረ እና የሰለጠነ ሰው መሆንን ከባህሉ ሥር መራቅን ይጠቁማል።
ከማንነት መነጠልን።
ዘመናዊነት…
ከዚህ በኋላ ግጥሙ ወደ ዋናው የዘመናዊነት ተቃርኖ ይገባል። “ለስልሻለሁ፣ ሠልጥኛለሁ፣ ሰይጥኛለሁ—አልሆንሽም” የሚለው አገላለጽ የግጥሙ እጅግ ጠንካራ ማዕከል ነው። ሰውየው በዘመናዊ ትምህርትና ሥልጣኔ ተለውጧል፤ ነገር ግን የመጣበትን ዓለም ሊሆን አልቻለም።
ይህ የግጥሙ አሳዛኝ ተቃርኖ ነው፤ ዘመናዊ ሆኗል፣ ነገር ግን ሥሩን አጥቷል። በዚህም ላይ “አጉል ሥልጣኔ ቆሞ” የሚለው ስንኝ ትልቁን ሐሳብ በአንድ ምስል ይይዘዋል። ሥልጣኔ በገጣሚውና በአቴቴ መካከል የቆመ ግድግዳ ይመስላል። ስለዚህ ግጥሙ ዘመናዊነትን በሙሉ አይክድም፤ ነገር ግን ሥልጣኔ ከማንነት ጋር ሲቆራረጥ “አጉል” እንደሚሆን ያጠይቃል።
የግጥሙ የቃላት ውበትም ይህንን የውስጥ ተቃርኖ በጣም ተሰሚ ያደርገዋል። ሎሬት ጸጋዬ በ“እርፍ–ተልም–አረም– ጉልጓሎ” የሥራ ቃላትን ከ“ፊደል–ሰለጠንኩ–ሥልጣኔ” ከሚሉ የዘመናዊ ሕይወት ቃላት ጋር ያጋጫል። በዚህ ቀላል የሚመስል የቃላት ምርጫ ውስጥ ትልቅ ሐሳብ ተደብቆ ይገኛል። “አጥንቴ ከአጥንትሽ ማዕድን” የሚለው ደግሞ ገጣሚውና አቴቴ መካከል ያለውን የደም እና የማንነት ትስስር ያጠናክራል። እሱ አቴቴን ቢርቃትም ከእርሷ የተለየ አይደለም፤ አጥንቱ ከአጥንቷ መነጨ፣ ነገር ግን ዘመናዊነት በመካከላቸው ቆመ። ይህ ነው ግጥሙን ከቀላል የባህል ናፍቆት ወደጥልቅ የማንነት ጥያቄ የሚያሸጋግረው።
በመጨረሻም፣ “አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ” ልጅነትን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን፣ የጠፋውን ማንነት መፈለግ ነው። አቴቴ በግጥሙ ውስጥ የኦሮሞ ባህል ምልክት ሆና ብቻ አትቀርም፤ የገጣሚው የልጅነት ዓለም፣ የተፈጥሮ ትዝታ፣ የሥር ምንጭና የጠፋ ማንነት መወከያ ትሆናለች። ዘመናዊነት ደግሞ ይህንን ዓለም ከእርሱ የለየ ኃይል ሆኖ ይታያል።
ስለዚህ ግጥሙ የሚያስታውሰን ትልቁ ጥያቄ፣ “ሰለጠንን ማለት ሥራችንን ነው የቀየርነው? ወይስ ራሳችንንም አጥተናል?” የሚለው ነው። ይህም ግጥሙን ከአንድ የኦሮሞ ባህል ማስታወሻ አልፎ፣ ባህልና ዘመናዊነት በሰው ውስጥ የሚገናኙበት ዘመን ተሻጋሪ የግጥም ሥራ ያደርገዋል።
በሠራዊት ከበበው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.