Fana: At a Speed of Life!

በዘላቂ የከተማ ልማት ጉዞዋ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘችው አዲስ አበባ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተማ ልማት ስኬት የሚለካው ከዘመናዊ ሕንፃዎችና መንገዶች ባሻገር ለነዋሪዎች በሚፈጥረው ምቹ የመኖሪያ ከባቢ፣ በሚያስገኘው የኢኮኖሚ ዕድልና በሚያስመዘግበው ዘላቂ ልማት ጭምር ነው።
ከዚህ አንጻር የአዲስ አበባ የከተማ ልማት ለውጥ የመንገድና የኮሪደር እንዲሁም የወንዝ ዳርቻዎች ልማት፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች መስፋፋት፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የትራንስፖርት ተደራሽነት በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚጠቀሱ ዋና ዋና የልማት መስኮች ናቸው።
በተለይም የኮሪደር ልማት የከተማዋን መሠረተ ልማት ከማሻሻል ባለፈ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን፣ የመናፈሻ ስፍራዎችን፣ የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችንና የንግድ አገልግሎቶችን በተቀናጀ መንገድ አካቷል። የወንዝ ዳርቻ ልማትም ከአካባቢ ጥበቃና ከከተማ ውበት ጋር የሚያያዝ አዲስ የልማት አቅጣጫ እየሆነ ነው።
ለአብነት ያህል በከተማዋ በቅርቡ የተከናወነው የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን–ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት 351 ሄክታር ስፋትና 10 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ የአረንጓዴ ስፍራዎችን፣ የመዝናኛና የስፖርት ቦታዎችን፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን እንዲሁም የኢኮኖሚ ተሳትፎ ዕድሎችን አካትቷል።
የእነዚህ ፕሮጀክቶች ጠቀሜታ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለንግድ እንቅስቃሴ፣ ለቱሪዝምና ለነዋሪዎች ማኅበራዊ ተሳትፎ አዳዲስ አማራጮችን መፍጠር ነው።
በትራንስፖርት መስክም የእግረኛና የብስክሌት መሠረተ ልማትን ከሕዝብ ትራንስፖርት ጋር ማቀናጀት የከተማዋን ተደራሽነትና የእንቅስቃሴ ቅልጥፍና ለማሻሻል የሚያግዝ አቅጣጫ ነው። ይህም የከተማ አገልግሎቶች ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በቀላሉ እንዲደርሱ ያስችላል።
በሌላ በኩል የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ማሳደግ፣ የነባር ሰፈሮችን መሠረተ ልማት ማሻሻል፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠበቅና የዲጂታል አገልግሎቶችን ማስፋፋት የዘላቂ ከተማ ግንባታ አስፈላጊ መሠረቶች ናቸው።
በእነዚህ እና በሌሎችም መመዘኛዎች መሠረት አዲስ አበባ ከተማ የ2024 የዓለም ከተሞች ቀን “የሻንጋይ አዋርድ” ሽልማትን ማሸነፍ ችላለች።
የከተማ ልማት ሥራዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመገምገም ከሚያስችሉ መለኪያዎች መካከል ዘላቂነት፣ አካታችነት፣ የነዋሪዎች ተጠቃሚነትና የከተማ መቋቋም አቅም ዋነኞቹ ናቸው።
በእነዚህ መስኮች የተመዘገቡት ውጤቶች የከተማዋን የልማት አቅጣጫ ከማሳየት ባለፈ በዓለም አቀፍ የከተሞች ልማት ደረጃ ውስጥ የሚኖራትን ተሳትፎ አጠናክረዋል።
የሻንጋይ ሽልማት በተባበሩት መንግሥታት የሰዎች ሰፈራ ፕሮግራም እና በቻይና መንግሥት በጋራ የተቋቋመ ዓለም አቀፍ የከተሞች ልማት ሽልማት ነው። ዓላማውም በዘላቂ፣ አካታችና የመቋቋም አቅም ባለው የከተማ ልማት ረገድ ውጤታማ ሥራዎችን ለሚያከናውኑ ከተሞች ዕውቅና መስጠት ነው።
ሽልማቱ ከተሞችን የሚገመግመው በሥራዎቻቸው ተጨባጭ ተፅዕኖ፣ ፈጠራ፣ ዘላቂነትና ከሁኔታዎች ጋር የመላመድ አቅም መሠረት ሲሆን በየዙሩም እስከ አምስት ከተሞች ይመረጣሉ።
በ2024 የሁለተኛው ዙር ሽልማት በተለይ አራት የልማት መስኮች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን እነሱም ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ የከተማ መልሶ ማልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል መሠረተ ልማት እና በከተማ አስተዳደር የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን ማሳደግ ናቸው።
በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ያገኘችው ዕውቅና የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን ማዘጋጀት፣ የተመጣጣኝ ቤቶችን አቅርቦት ማሳደግና በመረጃ ላይ የተመሠረተ አስተዳደርን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው።
የአዲስ አበባ የከተማ ልማት ሂደት አካላዊ ግንባታን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን፣ ማኅበራዊ ተጠቃሚነትንና የአካባቢ ጥበቃን በአንድ ላይ የማቀናጀት ጥረት ውጤት ነው።
በዓለም ከተሞች ቀን የሻንጋይ ሽልማት የተገኘው ዕውቅና የከተማዋን የልማት ልምድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ፣ የከተሞችን ተሞክሮ ለመለዋወጥና ለወደፊት የልማት ትብብር አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያግዝ ነው።
ዘላቂ ልማት የዛሬውን የነዋሪዎች ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለቀጣይ ትውልዶችም ምቹ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና ኢኮኖሚያዊ ዕድል የሚፈጥር መሠረት መጣል ለመሆኑ የአዲስ አበባ ተሞክሮ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
በምህረት ደምሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.