Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የ’ኢቪ’ አብዮት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EV) ሽግግር ስትራቴጂ በመተግበር ላይ ትገኛለች።

በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ በዓለም የመጀመሪያዋ የሆነችው ኢትዮጵያ ከጥር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ይህን ውሳኔ በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡

የሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ መሠረት እስከ 2030 ድረስ 500 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ መንገድ ለማስገባት እና 432 ሺህ ነባር የነዳጅ መኪኖችን ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር ግብ ተቀምጧል።

ብሉምበርግ ትናንት ባቀረበው ዘገባ፣ በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ መኪኖች ከሀገሪቱ አጠቃላይ የተሽከርካሪ ቁጥር 6 በመቶውን የሚሸፍኑ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ይህም ከዓለም አቀፍ አማካይ (4 በመቶ) የሚበልጥና ለአብዛኞቹ አዳጊ ሀገራት ሞዴል የሚሆን አስደናቂ ሽግግር መሆኑን አመልክቷል።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለነዳጅ ዘይት ግዢ እስከ 6 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ እንደምታወጣም እና ወደኤሌክትሪክ መኪኖች የሚደረገው ሽግግር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት እንደሚያስችል ዘገባው ጠቅሷል።

ይህም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የተነሣ ኢትዮጵያ በኪሎዋት ሰዓት አሥር ሳንቲም ገደማ በሆነ ርካሽና ታዳሽ የውኃ ኃይል የመጠቀም ዕድል እንደተፈጠረላት አመልክቷል።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ስትራቴጂ ለታዳጊ ሀገራት የኢነርጂ ሽግግር ትልቅ ሞዴል ሆኖ የሚታይና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈ ስትራቴጂ ነው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በተፈሪ መኮንን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.