የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለቀጣናው ሀገራት በተለይም የኤርትራን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል – የሰማያዊ ማዕበል ፓርቲ አባላት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለቀጣናው ሀገራት በተለይም የኤርትራን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል አሉ የሰማያዊ ማዕበል ፓርቲ አባላት።
የፓርቲው አባላት ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር አጀንዳ ቅቡልነት ያለው እና ለቀጣናው ወሳኝ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት በቀጣናው ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ደግሞ በኤርትራ ከፍተኛ መነቃቃት የሚፈጥርና እኩል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን አመልክተዋል።
የሰማያዊ ማዕበል ፓርቲ አባል አቶ ኤፍሬም ሃብተ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከኢትዮጵያ ባሻገር የቀጣናውን ሀገራት እንደሚጠቅም አስገንዝበዋል።
የጥያቄው ምላሽ ማግኘት ለኤርትራ ሕዝብም የገበያ ዕድልን ጨምሮ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባላት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥና በተለያዩ ምክንያቶች ከኤርትራ ሕዝብ ጋር የሚያመሳስሏት በርካታ ጉዳዮች እንዳሏትም ገልጸዋል።
ሌላው የፓርቲው አባል ደጀን ብርሃነ በበኩላቸው፤ የቀረበው ጥያቄ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ለሁለቱም ሀገራት በሚጠቅም መንገድ በመግባባት ጉዳዩን መፍታት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የኤርትራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ጋር በቴክኖሎጂ፣ በሰላምና ደኅንነት እንዲሁም በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች በጋራ በመሥራት ለሀገራቱ የጋራ ልማት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችል አስረድተዋል።
የሻዕቢያ አገዛዝ የኤርትራ ሕዝብ ከሀገሩ የተፈጥሮ ሀብት እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆን ከማድረግ ባለፈ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ግጭት በመፍጠር ሥልጣኑን ለማራዘም እየተጠቀመበት እንደሚገኝም ገልጸዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በሚዛን መኮንን