የዓለማችን እጅግ ፈጣኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው – ብሉምበርግ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት እያከናወነችው የሚገኘው ቁርጠኝነት የተሞላበት የኤሌክትሪክ ተሸካርካሪዎች አብዮት ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል፡፡
ታዋቂው የዜና አውታር ብሉምበርግ ለዕይታ ባበቃው ሰፊ ዘገባ፥ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለየት ያሉና ድፍረት የተሞላባቸው ርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ ትታወቃለች ብሏል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በካርቦን ልቀትና በነዳጅ ጥገኝነት ሳቢያ የሚታዩ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ፣ በርካታ የበለጸጉ ሀገራት እንኳን ያልደፈሩትን ቁርጠኛ ርምጃ በመውሰድ የዓለምን ትኩረት በመሳብ ላይ እንደምትገኝ ብሉምበርግ አትቷል።
በፈረንጆቹ 2024 ወዲህ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማገድ፤ ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የመሸጋገር ታሪካዊ ውሳኔ ማሳለፏን አስታውሷል።
ይህ ውሳኔ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ጥንካሬ የሚያረጋግጥና ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ታላቅ ድል ነው።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ 5 ቢሊየን ዶላር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለነዳጅ ግዢ ወጪ ስታደርግ መቆየቷን የጠቀሰው ዘገባው፤ ይህ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ጫና ለመቀነስና የኢኮኖሚ አቅምን ለማጠናከር ወሳኝ ነው ብሏል፡፡
በተጨማሪም ይህንን ከፍተኛ ወጪ በማስቀረት የሀገሪቱን የፋይናንስ አቅም በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በተለይም ሰፊው የህብረተሰብ ክፍልና የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች በወር እስከ 150 ዶላር የሚደርስ የነዳጅ ወጪ ማዳን መቻላቸው፤ የፖሊሲው ቀጥተኛ አዎንታዊ ተጽእኖ ማሳያ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ብሉምበርግ ዘገባውን ሲቀጥል፤ በፈረንጆቹ 2024 በአዲስ አበባ ከተመዘገቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
በሀገሪቱ በፈረንጆቹ 2022 7 ሺህ ብቻ የነበረው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር በ2025 ወደ 100 ሺህ ማደጉን በማንሳት፤ በዚህም ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ ሽግግር የዓለምን አማካይ እድገት መብለጧን ነው የጠቆመው።
ኢትዮጵያ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የምታደርገውን ፈጣን ሽግግር እውን ያደረገው ዋናው መሠረት ደግሞ 5 ሺህ ሜጋ ዋት ያህል ንጹህ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው ይላል ዘገባው።
ሀገሪቱ በዓለም ደረጃ በአነስተኛ ዋጋ 99 በመቶ ንጹህ ኃይልን ከሚጠቀሙ ጥቂት ሀገራት አንዷ መሆኗን በመግለጽ፤ ለዚህ የታዳሽ ኃይል ልማት አድናቆቱን ችሯል።
ይህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፖሊሲ ተሽከርካሪዎችን ከመግዛት ባለፈ የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ብሉምበርግ ያትታል።
እንደ በላይነህ ክንዴ ግሩፕ (ቢ.ኬ.ጂ) ያሉ ሀገር በቀል ኩባንያዎች የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ፤ በተለይም የቻይና ባለሙያዎችን ልምድ በመቅሰም በኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሙሉ በሙሉ የተሽከርካሪ መገጣጠም ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
ይህ አሰራር የሀገር ውስጥ አቅምን ከመገንባቱም በላይ ለዜጎች በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠሩንም ነው ዘገባው የሚያስረዳው።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት እቅዷ መሠረት በፈረንጆቹ 2033 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር 500 ሺህ 000 ማድረስና ከ2 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት አቅዳ እየሰራች ነው።
በመደመር መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት በአሁኑ ወቅት የኃይል መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋትና የመንገድ አውታሮችን የማጠናከር ሥራዎች ከየትኛውም ጊዜ በላይ በተፋጠነ ሁኔታ በመከናወን ላይ ናቸው።
እንደ ብሉምበርግ ያሉ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ለዓለም እየገለጡት የሚገኘው የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የእድገት ጉዞ፤ ሀገሪቱ የወደፊት ብሩህ ዘመንን እየገነባች መሆኗን የሚያረጋግጥ የኩራት ምዕራፍ ነው።
ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አብዮት ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብትና የፖሊሲ ቁርጠኝነት በመደመር እሳቤ በማስተባበር በአስደናቂ ፍጥነት እየተጓዘች እንደምትገኝ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በመልካም ፈቃዱ