ኢትዮጵያን የባህር በር ያሳጣትን ውሳኔ ማን ወሰነው?
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን ያጣችው በማን ውሳኔ ነው? ውሳኔውን ያሳለፈው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሆን? የምክር ቤቱን የውሳኔ ሰነዶች ስንመረምር ግን ይህንን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አናገኝም። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በዚህ ረገድ ውሳኔ አላሳለፈም።
ታዲያ የአንድን ሀገር ታሪክ፣ የኢኮኖሚ አቅምና የስትራቴጂክ ጥቅም የሚነካ እንዲሁም የሕዝብን ሕይወት የሚወስን እንዲህ ያለ ትልቅ ውሳኔ ማን አሳለፈው? ሕዝቡ ያልወሰነው፣ ተወካዮቹ ያልተወያዩበትና ካስፈጻሚው አካል በይፋ ያላፀደቀው ውሳኔ እንዴት ተፈጸመ?
አንድ ሀገር እንደ ባህር በር ያለ ወሳኝ ጥቅሟን ያጣችበት ሂደት በተቋማዊ ውሳኔና በሕጋዊ አሠራር የተመራ ካልሆነ፣ ይህ የሕጋዊነትና የተቋማዊ ተጠያቂነት ጥያቄን ያስነሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ወደብ አልባ መሆን ኢ-ፍትሐዊ የታሪክ ሂደት ሲያብራሩ፣ የውሳኔው ሂደት በሀገሪቱ ተቋማት ውስጥ ያልተካተተ መሆኑን አጉልተዋል። ይህም የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን ታሪካዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕጋዊነት፣ የተቋማዊ ኃላፊነትና የሀገራዊ ጥቅም ጥያቄም መሆኑን ያሳያል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማጣትን የሚያክል ነገር ያጣንበት መንገድ ህጋዊነት ችግር እንዳለ ማሳያው ተቋማት አልገቡበትም ሰሉ አመልክተዋል።
ባህር እና ባህር በር በጥንታዊ ታሪኳ ውስጥ ሥር የሰደደ፣ ከንግድ፣ ከባህልና ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ጋር የተሳሰረ እውነቷ የሆነው ሃገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ይህንን በታሪክ አጋጣሚ እና በጠላቶች ሴራ ያጣችውን የባህር በሯን ለማስመለስ ቁርጠኛ አቋም ይዛለች።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የዓባይን ጉዳይ ዘግታ ትኩረቷን ወደ ቀይ ባሕር አዙራለች በማለት የኢትዮጵያን ትኩረት አጽኖት ሰጥተው አመልክተዋል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት፣ እያደገ የመጣ የኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ ያላት ኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት ፍላጎቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የወደብ አልባነቷም በውጭ ንግድ ላይ ተጨማሪ ወጪ፣ የሎጂስቲክስ ችግርና የውጭ ወደቦች ጥገኝነት እንዲኖር አድርጓል።
በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ፣ ለትራንዚትና ለተያያዥ የሎጂስቲክስ አገልግሎቶች የሚወጣው ወጪም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና ይፈጥራል። ይህ የንግድ ተወዳዳሪነትን ከመገደቡም በላይ በአቅርቦት ሰንሰለትና በስትራቴጂክ እቃዎች አቅርቦት ላይ ተጨማሪ ተጋላጭነት ይፈጥራል።
ስለዚህ የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የንግድ መሸጋገሪያ ብቻ ሳይሆን ከኢኮኖሚ ደህንነት፣ ከስትራቴጂክ ነፃነትና ከቀጣናዊ ተሳትፎ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው።
በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ መሠረት ወደብ አልባ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስና የመጓጓዣ መብት አላቸው። በተለይም የባሕር ሕግ ስምምነት (UNCLOS) አንቀጽ 125 ወደብ አልባ ሀገራት የመጓጓዣ ነፃነትን ይደነግጋል። ሆኖም ይህ መብት በተግባር የሚፈጸመው በሚመለከታቸው ሀገራት መካከል በሚደረግ ስምምነትና በሕጋዊ ማዕቀፍ መሠረት ነው።
ኢትዮጵያም ወደ ባሕር የምታደርገው ጉዞ የትናንት ታሪክ ማስታወሻ ብቻ ሳይሆን የዛሬና የነገ ሀገራዊ ጥቅም መሠረት ነው። ይህንን ጥያቄ ከታሪካዊ ቁርኝት፣ ከኢኮኖሚያዊ ፍላጎትና ከቀጣናዊ ትብብር አንጻር ማየት ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም የባሕር በር ጥያቄን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ ማዕቀፍና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማሳካት ያለውን አቋም እያሳወቀ ይገኛል።
በመጨረሻም የሚነሳው ጥያቄ ይህ ነው፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት የታሪክ ሂደት ምን ነበር? የዚያ ሂደት ሕጋዊ መሠረትና ተቋማዊ ተጠያቂነትስ ምን ይመስላል? እነዚህ ጥያቄዎች በታሪካዊ ማስረጃና በሕጋዊ ሰነዶች ላይ ተመሥርተው ሊመለሱ ይገባል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን በግጭት ሳይሆን በሕግ፣ በዲፕሎማሲና በጋራ ተጠቃሚነት ማሳካቷ ለሀገሪቱም ሆነ ለቀጣናው ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ መንገድ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንዳሉት “ ማንም ወደደም ጠላም ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም !”
በሶስና አለማየሁ