ኢትዮጵያ በኮፕ – 31
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ባለው ኮፕ – 31 የራሷን ፓቪሊዮን በመክፈት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታከናውናቸውን ተግባራትና የአረንጓዴ ልማት ልምዶቿን ለዓለም እያስተዋወቀች ትገኛለች።
ይህ ተሳትፎ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ለምታስተናግደው ኮፕ – 32 የምታደርገው ዝግጅት አካል ነው።
ፓቪሊዮኑ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ፣ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ በታዳሽ ኃይል ልማትና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ያከናወነቻቸውን ሥራዎች የምታቀርብበት ዓለም አቀፍ መድረክ ነው።
በተጨማሪም ለኮፕ 32 የተያዙ አጀንዳዎችን ከወዲሁ ለማስተዋወቅ ከተለያዩ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የጋራ መግባባት ለመፍጠርና የጉባኤውን የድርድር ሂደት ለማጠናከር የሚያግዝ የዲፕሎማሲ መድረክ ነው።
የአየር ንብረት ጉባኤዎች የሀገራት የአካባቢ ጥበቃ ጥረቶችን ከማቅረብ ባለፈ፤ በበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ፣ የአየር ንብረት ጉዳትን የመቋቋም፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በፋይናንስ ድጋፍ ላይ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚፈጸሙባቸው ወሳኝ መድረኮች ናቸው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በኮፕ – 31 ያላት ተሳትፎ ለኮፕ – 32 የዝግጅት ልምድ ከመቅሰም ባለፈ በሚቀጥለው ዓመት በምታስተናግደው ጉባኤ የሚነሱ ጉዳዮች በድርድር ሰነዶችና በዓለም አቀፍ መግለጫዎች ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኙ ከወዲሁ የሚደረጉ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን ያካትታል።
ጉባኤው እና የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን አጋርነት ለማስፋት፣ የአየር ንብረት ፋይናንስና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማሰባሰብ፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማበረታታትና ለዘላቂ ልማት የሚያግዙ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ የሚያስችል ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ፓቪሊዮኑ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብት፣ የማዕድንና የተፈጥሮ ሀብት አቅም፣ የአካባቢ ጥበቃ ተሞክሮና የሥልጣኔ ቅርሶች ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥራል።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነቷን ለመቀነስና ለአካባቢ ጥበቃ የሚያግዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች።
በተለይም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስና የካርበን ልቀትን ለመቆጣጠር የሚያግዝ ብሔራዊ ጥረት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ከውሃ፣ ከነፋስ፣ ከጸሐይ እና ጂኦተርማልን ጨምሮ የታዳሽ ኃይል ምንጮችን ስብጥርንና አቅምን በማስፋፋት የኢኮኖሚ ዕድገትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በማጣጣም ዘላቂ ልማቷን እያፋጠነች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የኮፕ – 32 አዘጋጅ መሆኗ የአፍሪካን የአየር ንብረት ተጋላጭነት፣ የፋይናንስ ችግርንና የፍትሐዊ የልማት ጥያቄዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ለማስቻል አጋጣሚ ይፈጥርላታል።
የኮፕ – 31 ተሳትፎዋም ይህንን የወደፊት ኃላፊነት በተገቢው ሁኔታ ለመወጣት የሚያስፈልገውን የልምድ ልውውጥ፣ ወዳጅነትን ለመፍጠርና የቅድመ ዝግጅት ሥራ የምታጠናክርበት መድረክ ነው።
በምህረት ደምሴ