የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን የመቀነስ ተግባር የሀገራትን ቅንጅት ይጠይቃል – ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን የመቀነስ ተግባር የሀገራትን ቅንጅትና ትብብርን ይጠይቃል አሉ የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን፡፡
በቱርክዬ አናታሊያ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ ኮፕ31 የመሪዎች ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።
ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በፓሪሱ ስምምነት መሰረት ለአየር ንብረት ለውጥ የሚደረጉ የፋይናንስ ድጋፎች እየጨመሩ መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡
ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ከባድ ስጋት ተጋርጦባታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ምርጫችን ሁለት ነው፤ ወይ ቆመን ሁኔታውን መቀበል ወይም ደግሞ አስቀድሞ መከላከል ብለዋል።
ቱርክዬ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የገባቻቸውን ቃል ኪዳኖች ወደ ተግባር ለመለወጥ ጥረት እያደረገች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ለአብነትም የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ለአረንጓዴ ሽግግር ቅድሚያ መስጠቷን እንዲሁም የኢነርጂ አጠቃቀም ውጤታማነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን እየተገበረች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ሀገራቸው ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የትራንስፖርት አማራጮችን እያሰፋች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በቱርክዬ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ አቅም ውስጥ የታዳሽ ኃይል ምንጮች ድርሻ ከ60 በመቶ በላይ መድረሱን አመላክተዋል፡፡
በውሃ አጠቃቀም ውጤታማነት መርሐ ግብር አማካኝነት ቱርክ የውሃ ብክነትን ለመቀነስ የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል የአንድ ወገን ድርሻ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ሀገራት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ