Fana: At a Speed of Life!

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን የልማት ተልዕኮዎችን በሚያሳካ መንገድ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል – አፈ ጉባኤ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) 21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የመንግሥት የልማት ተልዕኮዎች በሚያሳካ መንገድ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሙፈሪሃት ካሚል።
አፈ ጉባኤዋ በዓሉን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ቀኑ “በብዝሃነት የደመቀች በምክክር የፀናች ሥልጡን ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ይከበራል።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለ5 ቀናት እንደሚከበር እና እነዚህም ቀናት የወንድማማችነት ቀን፣ የአብሮነት ቀን፣ በዓሉን ለሚያስተናግዱ ክልሎች አንድ ቀን የሚሰጥ በመሆኑ የዘንድሮው የኦሮሚያ ቀን፣ የምክክር ቀን እንዲሁም ሕዳር የኢትዮጵያ ቀን ተብሎ ተሰይሟል።
የዘንድሮው መሪ ሀሳብ የጋራ ቃል ኪዳን፣ የጋራ ዕቅድና የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር፤ ብዝሀነት ሀብት፣ ምክክር የሥልጣኔ መንገድ፣ ሥልጡን ማህበረሰብን ደግሞ የግቡ መዳረሻ ያደረገ ነው።
ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች አምራች፣ መሪ እና ሥልጡን ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችል የ25 ዓመት የትውልድ ፍኖት መቀረጹን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የብዝሃ ማንነት ሀገር ናት ሲባል በብዙ ማንነቶች የደመቀች ማለታችን ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ ብዝሃነት በአግባቡ መመራት ከቻለ ለፈጠራ፣ ልህቀትና ሀገራዊ ሽግግር ወሳኝ ሀብት ነው ብለዋል።
ስለሆነም ኢትዮጵያውያን የብዝሃነት ጸጋችንን በመንከባከብና ለልማት በማዋል ለዕድገታችን ምንጭ ልናደርገው ይገባል ነው ያሉት።
21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የመንግሥት የልማት ተልዕኮዎች በሚያሳካ መንገድ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ስለሆነም ቀኑ በዓልን ከማክበር ባሻገር ትልቅ ሀገር ለማሻገርና ዘላቂ ብልፅግናን ለማረጋገጥ መሰረት እንደሚጥል አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በሥልጡን የምክክር ባህል የተጣለውን መሰረት ወደ ላቀ ምዕራፍ የማሸጋገር ተልዕኮውን መወጣት አለበት ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.