Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ፍሬ – ኮፕ32

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ በዘመናችን የሰው ልጅ ከተጋረጡበት ትላልቅ ፈተናዎች መካከል ቀዳሚው ነው።

ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ተግባራዊ መፍትሄን ለማፍለቅ የተባበሩት መንግሥታት በየዓመቱ የሚያካሂደው የአየር ንብረት ጉባኤ ኮፕ ወሳኝ መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ንቁ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚና ስትጫወት የቆየች ሲሆን፤ በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደውን 32ኛውንጉባኤ (ኮፕ32) በአዲስ አበባ ታስተናግዳለች፡፡

ይህም በተለይም በመደመር መንግሥት የተከናወኑ የሀገሪቱ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ፍሬ ማፍራት መጀመራቸውን ያመላከተ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በኮፕ ጉባኤዎች ላይ ከተሳትፎ ባለፈ የአፍሪካን እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ፍላጎት በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ሚና ያላት ሲሆን፤ በተለያዩ ወቅቶች በኮፕ ጉባኤዎች ላይ የአፍሪካን ተደራዳሪዎች ቡድን በመምራት ቁልፍ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የምታቀርባቸው ሀሳቦች በተግባር የተደገፉ ናቸው፤ በፈረንጆቹ 2011 ያጸደቀችው “ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ” በአፍሪካ ቀዳሚው ፖሊሲ ሆኖ ተመዝግቧል።

በቅርብ ዓመታት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል ችላለች፡፡

በተጨማሪም በታዳሽ ኃይል ልማት በተለይም የውኃ፣ የንፋስና የፀሐይ ኃይል የልማት ተግባራት እንዲሁም ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የተደረገው ሽግግር ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ልማት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ አድርጓታል።

የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በቀጣዩ የኮፕ ጉባኤ ከ190 በላይ ሀገራትን በማስተናገድ የዓለም የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ማዕከል ትሆናለች፤ ኢትዮጵያም የአፍሪካን የፋይናንስና የፍትሕ ጥያቄ በበላይነት ትመራለች።

ሁነቱ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የሚገኙ የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ግብርና ፕሮጀክቶችን በቀጥታ ተመልክተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሰፊ በር ይከፍታል።

የኢትዮጵያና የኮፕ ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሠረተ፣ ረጅም ታሪክ ያለውና በተጨባጭ ውጤቶች የታጀበ ነው፤ ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የገነባችው የአረንጓዴ ልማት ስኬትና የዲፕሎማሲ ጥንካሬ ለኮፕ32 ጉባኤ አስተናጋጅነት አብቅቷታል።

ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘላቂ የአየር ንብረት መፍትሔዎችን የምታበረክትበት ታሪካዊ አጋጣሚ ይሆናል።

#ኢትዮጵያ #ኮፕ_32_ኢትዮጵያ #COP31 #COP32 #COP32ETHIOPIA #fanamediacorporation

በትዕግስት ግዛቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.