Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ እየተካሄደ ያለው የተሃድሶ ሥራ የሰላምና የልማት መሠረት ነው – አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው የቀድሞ ታጣቂዎችን የማቋቋምና የተሃድሶ ሂደት ለክልሉ ዘላቂ ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ ልማት መሠረት ንነው አሉ በኢትዮጵያ የዴንማርክ እና የስዊድን አምባሳደሮች።

አምባሳደሮቹ በክልሉ የሚገኘውን የተሃድሶ ማዕከል በጎበኙበት ወቅት በማዕከሉ እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶችን የተመለከቱ ሲሆን፣ ከቀድሞ ታጣቂዎች ጋርም ውይይት አድርገዋል።

በጉብኝቱ ወቅት በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሩፕ በትግራይ ክልል ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማስጀመር ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ከቀድሞ ታጣቂዎች ጋር ባደረጉት ውይይትም፣ ታጣቂዎቹ ለግጭትና ለጦርነት ጀርባቸውን በመስጠት የሰላምን መንገድ መምረጣቸውና የማኅበረሰቡ ንቁ አምራች አባላት ለመሆን መወሰናቸው ለክልሉ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እጅግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ማግኑስ ሌናርትሰን በበኩላቸው በማዕከሉ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ስፋት እና የአገልግሎት አሰጣጥ አስደናቂ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሀገራቸው ስዊድን በመላው ኢትዮጵያ ለሚካሄደው የተሃድሶ ሂደት የረጅም ጊዜ አጋር በመሆኗ እንደምትኮራ የገለጹት አምባሳደሩ ጉብኝቱ ስለ ክልሉ የወደፊት ተስፋና እምቅ የሰው ኃይል አቅም ብሩህ እይታ እንደፈጠረላቸው አመላክተዋል።

አክለውም ስዊድን በትግራይ ክልል ቀጣይነት ያለው መረጋጋት፣ ሰላም እና ብልጽግና ለመገንባት የምታደርገውን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣችቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.