አዲሱ የብር ለውጥ ከተጀመረ ወዲህ 14 ቢሊየን ብር ወደ ባንክ ገቢ መደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣መስከረም 23 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ አዲሱ የብር ለውጥ ከተጀመረ ወዲህ 14 ቢሊየን ብር ወደ ባንክ ገቢ መደረጉን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
አዲሱ የብር ለውጥ ከተጀመረ ባሉት 14 ቀናት ውስጥ ብቻ 580 ሺህ ዜጎች አዲስ የሂሳብ አካውንት ሲከፍቱ ÷ ከባንክ ውጭ የነበረ 14 ቢሊዮን ብርም ወደ ባንክ መግባቱን ብሔራዊ ባንክ ገልጿል።
67 ቢሊየን አዲሱን ብር በመላ አገሪቱ ባሉ 99 ነጥብ 9 በመቶ የባንክ ቅርንጫፎች ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲዳደረስ መደረጉን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ገልፀዋል።
የብር ለውጡ ያስፈለገበት አንዱ ዓላማ ከባንክ ውጭ ያለን ገንዘብ ወደባንክ የማስመለስ ጉዳይ እንደነበር ያስታወሱት የባንኩ ገዥ ÷ ከዚህ አንጻር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሄንን ያህል ገንዘብ ወደ ባንክ ስርዓቱ መመለሱ የዓላማውን መሳካት ያሳያል ብለዋል።
የብር ለውጡ ሌላኛው ዓለማ የባንክ አገልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ይናገር÷ አዲስ የባንክ ሂሳብ ከተከፈቱት 580 ሺህ ዜጎች በተጨማሪ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች አካውንት ይከፍታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ህብረተሰቡ በተያዘው የጊዜ ገደብ ውስጥ በእጁ ያለውን አሮጌ የብር ኖት በአዲሱ መቀየር እንዳለበትም ዶክተር ይናገር ማሳሰባቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።