Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ስብሰባውን አጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቋል፡፡

ምክር ቤቱ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ነው ያካሄደው፡፡

በዚህም ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የኢፈዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የቀረበን የድጋፍ ሞሽን አድምጧል፡፡

ምክር ቤቱም የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን ካዳመጠ በኋላ የፕሬዚዳንቷን ንግግር የተቀበለው ሲሆን ሞሽኑ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማብራሪያና ምላሽ ከሰጡ በኋላ እንዲጸድቅ ወስኗል፡፡

በመቀጠልም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የንግድ ሕግ ረቂቅ አዋጅን ከመረመረ በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ለንግድና ለኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቶታል፡፡

እንዲሁም የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለገቢዎች በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ዓላማ ለማዋል የተደረገውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅንም መርምሯል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ረቂቅ አዋጁን ለውጭ ግንኙነት እና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቶታል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የኢፊዴሪ የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ህግ ረቂቅ አዋጅን መርምሯል፡፡

ይህ ረቂቅ አዋጅ ለ13 ዓመታት የቆየውን የወንጀል ህግ አሻሽሎ የመጣ መሆኑን ምክር ቤቱ ያነሳ ሲሆን ከ400 በላይ አንቀጾች ተካተውበታል፡፡

የወንጀል ህጉ ላይ የነበሩ በርካታ ግድፈቶችና ከወቅቱ ጋር የማይሄዱ ነጥቦችም የተሻሻሉበት ረቂቅ አዋጅ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

ምክር ቤቱ ይህንን መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለህግና ፍትህ ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

በኃይለየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.