በደሴ ፣ኮምቦልቻ እና ድሬዳዋ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በደሴ ፣ኮምቦልቻ እና ድሬዳዋ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡
ውይይቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከርና ህዝቡ በህወኃት በሚነዙ አፍራሽ እና መሰረት የሌላቸው መረጃዎች ሳይደናገር በአብሮነት የመኖር እሴትን እንዲያጠናክር ያለመ ነው ተብሏል።
የሳይንሰ እና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ነብዩ ሱሁል ሚካኤል ውይይቱን መርተዋል።
በከተሞቹ የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆች ነባራዊ ሁኔታውን ተገንዝበው ኢህአዴግ ከግንባር ወደ ውህደት የመጣበትን አስፈላጊነት እንዲረዱ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቧል።
ከዚህም ባሻገር የብልጽግና ፓርቲ ፍልስፍና፣ ዓላማ እና የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም ህወኃት እየሄደበት ያለውን አፍራሽ አካሄድ ግልጽ የሚያደርጉ ነጥቦችም ቀርቧል።
ውይይቱ የትግራይ ህዝብ ከብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ ሂደት አንጻር እንዴት እንደሚታይ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ማተኮሩ ነው የተገለጸው።
በተመሳሳይ በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች የፌዴራል መንግስትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎች የትግራይን ህዝብ ለመጉዳት ያለመ ነው እያሉ ህዝቡን ለማደናገር ጥቂት በህወኃት አመራሮችና ሚዲያዎች የከፈቱት ዘመቻ ላይ የውይይትና ምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ግልጽነት ሊፈጠር ይገባል ብለዋል፡፡
የህወኃት አመራሮች የትግራይን ህዝብ አይወክሉም ያሉት ተሳታፊዎቹ የትግራይን ሕዝብ ባልተገባ መንገድ ቀስቅሰው ወደ ጦርነት ለማስገባት የሚያደርጉትን ውዥንብር የፌዴራል መንግስት እርምጃ በመውሰድ ህገ ወጦችን ከህዝቡ መነጠል አለበትም ብለዋል፡፡
በአንድነት ናሁሰናይ