Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ቦርድ ከኦነግ አመራር አባላት የቀረቡለትን አቤቱታዎች አስመልክቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባርን /ኦነግ/ አመራር አባላት የቀረቡለትን አቤቱታዎች አስመልክቶ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ፡፡

ቦርዱ በእነ አቶ ዳውድ ኢብሣ የሚመረጥ/የምትመረጥ አንድ፤ በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመረጥ/የምትመረጥ ሌላ አንድ፤ እንዲሁም እነዚህን ሁለት በባለጉዳዮቹ የሚመረጡትን ባለሙያዎች በሰብሳቢነት የሚመራ/የምትመራ ሌላ አንድ ባለሙያ መርጦ በመመደብ የባለሙያዎች ጊዜያዊ ጉባኤ እንዲቋቋም ትናንት ባካሄደው ስብሰባ መወሰኑን ነው የገለጸው፡፡

በዚህ መሰረት በሁለቱ አካላት እና በቦርዱ የተመረጡ ባለሙያዎች ጉዳዮን አጣርተው በሚያቀርቡት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

ቦርዱ ከኦነግ ፓርቲ አመራር አባላት የአመራር ለውጥ እና እገዳን አስመልክቶ የተለያዩ አቤቱታዎች ሲደርሱት እንደነበር አስታውሷል፡፡

በዚህም እነ አቶ አራርሶ ቢቂላ ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ሁለት ደብዳቤዎች የጻፉ ሲሆን የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በፓርቲው ሊቀመንበር በአቶ ዳውድ ኢብሳ ላይ የእግድ ውሣኔ አስተላልፏል ሲሉ ለቦርዱ በማሳወቅ ቦርዱ ውሳኔውን እንዲያጸድቅላቸው መጠየቃቸውን ነው የጠቀሱት፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ዳውድ ኢብሣ በፈረንጆቹ 08/10/2020 በፃፉት ደብዳቤ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በሆኑት አቶ አራርሶ ቢቂላ፣ አቶ ቶሌራ ተሾመ፣ አቶ አቶምሣ ኩምሣ እና የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት የሆኑት አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና አቶ አርብቾ ዲማ እስሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ ስለተወሰነ ይኸው ውሳኔ በቦርዱ እውቅና እንዲሰጠው መጠየቃቸውን ቦርዱ አስታውቋል፡፡

ቦርዱም ይህንኑ በፓርቲው አባላት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት የሚያስረዱትን ከዚህ በላይ የተገለፁትን ደብዳቤዎችና ሌሎች የጽሑፍ አቤቱታዎችን ትናንት ባካሄደው ስብሰባ መመርመሩን ነው የገለጸው፡፡

በፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል አለመግባባት ሲከሰት እና ለቦርዱ አቤቱታ ሲቀርብለት በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት ጉዳዩን ተመልክቶ የውሣኔ ሃሣብ የሚያቀርብ የባለሙያዎች ጉባኤ የማቋቋም ሥልጣን እንዳለው ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.